ባሕር ዳር፡ መስከረም 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የህልውና ዘመቻው በሚጠይቀው ልክ እና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚያስችል ሃብት እየተሰበሰበ አለመሆኑን ዛሬ እያካሄደ በሚገኘው ውይይት አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርእስ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር) ሁሉም ዜጋ በጦር ግንባር ሕይወታቸውን እየሰጡ ለሚገኙ የጸጥታ ኃይሎችንና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በሃብት አሰባሰብ የመንግሥት ሠራተኞች ጥሩ አፈጻጸም ቢኖራቸውም ከነጋዴው፣ ከገጠር እና ከከተማ ነዋሪዎች የተሰበሰበው ጥሬ ገንዘብ የህልውና ዘመቻው በሚጠይቀው መጠን አይደለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ወረራ ባልተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን የፈጸመውን ውድመት ሊያካክስ የሚችል ሃብት በመስጠት ለወገን አለኝታነትን ማሳየት እንደሚገባ ዶክተር ፋንታ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበባው ውቤ በክልል ደረጃ ለህልውና ዘመቻው ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገቢ ሲሰበሰብ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ አሰባሰቡ ግን በሚጠበቀው ልክ ባለመሆኑ ችግሩን መፍታት እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡
አቶ አበባው አሰባሳቢ ኮሚቴውም ከውይይት በኋላ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ሃብት በቁርጠኝነት ለመሰብሰብ ይሠራል ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ኀላፊው ማብራሪያ የሥራ ኀላፊዎችም መጪው ጊዜ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ሰፊ ሥራ የሚሠራበት መሆኑን በመገንዘብ ሃብት በመሰብሰብ ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል፤ ጎን ለጎን ደግሞ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የአካባቢው ወጣቶችን በማነቃቃት የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅና የህልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ንግድ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ገነት አሰፋ እንደ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የተሰበሰበው ገቢ ጥሩ ቢሆንም በቀጣይ ሁሉንም ተደራሽ በማድረግ ሃብት መሰብሰብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ለዚህም ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴው በትጋት ይሠራል ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡም የተጠየቀውን ለመስጠት የማይሳሳ ነው፤ የሕልውና ዘመቻውን በድል ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ