የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት አካላት በሠላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መሥራት አንዳለባቸው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ አሳሰቡ፡፡

0
72

የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት አካላት በሠላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር መክረዋል፡፡ ውይይቱ ደግሞ የሃይማኖት መቻቻልን፣ የአምልኮ ቦታዎችን አጠቃቀም፣ በሕግ እና ሥርዓት አከባበር ዙሪያ እና የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ግንኙነት የተመለከተ ነው፡፡

ለሃይማኖት አባቶች እና ለክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የመወያያ ሐሳብ ያቀረቡት የክልሉ ርእስ መሥተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ የሃይማኖት አባቶች ትውልዱን በሃይማኖት አስተምሮ በመቅረፅና ለሠላሙ ከመንግሥት ጎን ቆመው መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

የሃይማኖት አምልኮ ቦታዎች አጠቃቀም ጋር የሚነሱ ችግሮችን ደግሞ ዜጎች አንዱ ሃይማኖት የሌላውን ሃይማኖት በማይገፋ መልክ ተመካክረው መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የሃይማኖትን ብዘኃነት መረዳትም ለሠላም መረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ያስረዱት የክልሉ ርእሰ መሥተዳደር የሃይማኖት አባቶች እና መንግሥትም በጋራ ተጠናክረው መሥራት ሲችሉ ደግሞ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አረጋግጠዋል፡፡ የሃይማኖት መቻቻልን፣ የአምልኮ ቦታዎችን አጠቃቀም፣ በሕግ እና ሥርዓት አከባበር ዙሪያ እና የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማት ግንኙነትን በተመለከተም ከሃይማኖት አባቶች ጋር በነበረው ውይይት መግባባት ላይ እንደተደረሰ ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖቶች ፎረም ደግሞ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት በየሦስት ወር እየተገናኘ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርግ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም ደግሞ የሃይማኖት መሪዎች እንደመሪነታቸው፣ መንግሥት ደግሞ እንደመንግሥት ሠላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ማስፈንና ማንም ያለስጋት የሚኖርባት አገር መፍጠር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ “ሁሉም እንደየሃይማኖቱ በራሱ እምነት ላይ ተመሥርቶ ትውልዱን በሥነ ምግባር መቅረፅ አስፈላጊ ነው፤ ከክልሉ ባለስልጠናት ጋርም በመግባባት ላይ ተደርሷል” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በዘርፉ አጠናክራ እንደምትሠራና ሌላውም መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሁሉም “የእኔ ብቻ” ከሚለው አስተሳሰብ በመውጣት የኛ በሚል አመለካከት በፍቅር እና በሠላም መኖር እንዳለበት ብፁዕነታቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ “የጥንት አባቶቻችን የሙስሊም መስጅድ ሲሠራ በጉልበት እና በሐሳብ አግዘዋል፤ ለዓለምም ተምሳሌት ሆነዋል፤ ይህ ትውልድም የአባቶቻችንን ታሪክ መድገም አለበት” ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰይድ መሐመድ ደግሞ አንዱ ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት ጋር በጋራ መሥራት እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የፀጥታ ጉዳይ ደግሞ ከመንግሥት ጋር በጋራ ተባብረው የሚሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሮች እንኳን ቢፈጠሩ በውይይት መፍታት እንደሚቻል መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡ ሙስሊሙ ኅበረተሰብም ለሠላሙ ቅድሚያ በመስጠት ለሀገር አንድነት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አባ አብነት አበበ ደግሞ ሠላም ለማምጣት በጋራ ተግባብቶ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ዕውቅና ከሰጧቸው ሰዎች ውጭ ሰዎች ማስተማር እንደሌለባቸውም ገልጸዋል፡፡ ‘‘በጓሮ በመግባት ችግር የሚፈጥሩ አካላትንም ማጣራት እና እንዲሰተካከሉ መምከር ይገባል’’ ብለዋል አባ አብነት፡፡

የሰሜን ምዕራብ ክልል ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ዋና ጸሐፊ መጋቤ ገብሬ አሰፋ ደግሞ “በክልሉ ሠላም ለማምጣት የክልሉ መንግሥት እና የሃይማኖት አባቶች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል” ብለዋል፡፡ መንግሥት ከአምልኮ ቦታዎች ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ሕግ እና ሥርዓት ተከትሎ መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here