ዝናቡ ቀጣይነት ስለሚኖረው ጥንቃቄ እንዲደረግ ማዕከሉ አሳሰበ፡፡

0
60

ባሕር ዳር፡ መስከረም 07/2013ዓ.ም (አብመድ) የዝናቡ ስርጭቱ እስከ መስከረም መጨረሻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የምዕራብ አማራ ሚቲዮሮዎሎጅ አገልግሎት ማዕከል አስታወቀ፡፡

ባለፉት ወራት በክልሉ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ተከስቷል፡፡ በቀጣይ ቀናትም በምዕራብ አማራ አንድ አንድ ቦታዎች ላይ አልፎ አልፎ በሚከሰተው ከባድ ዝናብ የተፈጥሮ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድርግ እንደሚገባ ማዕከሉ አስጠንቅቋል፡፡

በማዕከሉ የትንተና፣ ትንበያ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ እንደግ አንለይ እንደገለጹት በክልሉ እስከ መስከረም መጨረሻ በሁሉም ቦታዎች ከቀላል እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል፡፡ በተለይም ደግሞ በምዕራብ አማራ ምዕራብ ጎጃም፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተወሰኑ ቦታዎች ላይ አልፎ አልፎ በቀን ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በፀሐይ ኃይል የታገዘ የደመና ክምችት በረዶ የቀላቀለ ዝናብ እና ነጎድጓድ እንደሚከሰትም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ በሚፈጠረው ከባድ ዝናብ በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ነው ባለሙያው ያስገነዘቡት፡፡

የሚፈጠረው የዝናብ መጠን በደረሱ ሰብሎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም በቀጣይ ሊለሙ ለሚችሉ እንደ ጓያ፣ ሽምብራ እና ሌሎች ሰብሎች እና ዘገይተው ለተዘሩ ሰብሎች መልካም አጋጣሚ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ የደረሱ ሰብሎችን ካሉም ቀድሞ መሰብሰብ እንደሚገባ ባለሙያው መክረዋል፡፡

ባለሙያው እንደገለጹት በምሥራቅ አማራ አልፎ አልፎ ቀላል እና መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ በአካባቢውም ዝናብ አጠር በሆኑ ቦታዎች አልፎ አልፎ የሚኖረውን ዝናብ በማቆር አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሚቻልም አቶ አንለይ ገልጸዋል፡፡

የአየሩ ሁኔታ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚቀያየር በመሆኑ ዓለም ዓቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና አካባቢያዊ የሜቲዮዎሮሎጅ ትንበያዎችን መረጃ መሠረት በማድርግ በቀጣይ ለማኅበረሰቡ መረጃዎችን እንደሚያደርሱ ባለሙያው ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here