“ዝምተኛ ጀግኒት” ሴት የአማራ ፋኖ

2318
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 02 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) ክንደ ብርቱ፣ አልሞ ተኳሽ፣ ብዙ በማውራት ሳይሆን በተግባር ጠላትን የምታሸብር፣ ወጣት የሴቶች ጀግና የአማራ ፋኖ ታድላ ስማቸው ትባላለች። በአሁኑ ወቅት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ጋር በመቀላቀል አሸባሪውን በመደምሰስ ላይ ትገኛለች። ለትግሉ ያነሳሳት ደግሞ አሸባሪው ቡድን ሀገር ለማፍረስ አልሞ መነሳቱ፤ በአማራ ሕዝብ ላይ የማወራርደው ሒሳብ አለኝ ብሎ ወረራ በፈጸሙ እንዲሁም በምትኖርበት አካባቢ ቀደም ሲል በኅብረተሰቡ ሲያደርስ የቆየው ግፍ መሆኑን ተናግራለች።
“አሸባሪው ትህነግ በአገዛዝ ዘመኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ መዥገር ተጣብቆ ከባድ በደል ፈጽሟል፣ አሳዷል፣ አስሮ አኮላሽቷል፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ከተባረረ በኋላም የሉዓላዊነት መገለጫ በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈጽሟል” ያለችው ፋኖ ታድላ ወራሪውን አሸባሪ ቡድን ለመታገል በጠገዴ ወረዳ ስትሠራ የነበረችውን የሆቴል ሥራ በመተው በ2007 ዓ.ም ወደ አማራ ፋኖ መግባቷን ተናግራለች።
አሸባሪው ቡድን ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የእሱ አባል ያልሆነ ሰው ሠርቶ እንዲለወጥ አይፈልግም ያለችው ፋኖ ታድላ ታታሪ ሠራተኞችንም የተለያዩ ሥሞችን እየሠጠ እግር በእግር ተከታትሎ ያጠፋል፤ ሰርተው እንዳይለወጡ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያለችው። በጠገዴ ወረዳ በሆቴል ሥራ ላይ እያለች በማታውቀው ጉዳይ “የግንቦት ሰባት አባልነሽ” በማለት ከሥራ እንዳገዷት ተናግራለች። ከሥራ ማገድ አልበቃ ብሏቸው ድብደባ፤ እስር እና እንግልት አድርሰውብኛል ነው ያለችን።
አሸባሪው ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሠው በደል ታሪክ ይቅር አይለውም ያለችው ፋኖ ታድላ ከእስር ከተፈታች በኋላ ደግሞ አገዛዙን በመቃወም ጫካ ውስጥ በርካታ ዓመታትን እንዳሳለፈች ተናግራለች።
አሸባሪው ትህነግ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሀገር ኩራት በሆነው በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሠንዘሩን ተከትሎ መንግሥት ያደረገላትን ጥሪ በመቀበል በሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ ወረዳ አካባቢ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ጋር በመሰለፍ ቡድኑን ድባቅ መምታት እንደተቻለ ገልጻለች።
ፋኖዋ ጀግና እንዳለችው በጀግኖች አባቶች ስም የተደራጀው የአማራ ፋኖ ከመንግሥት የጸጥታ ኀይል ጋር በመቀናጀት አሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደስታውን ያበስራል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው – ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ