ዛሬ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣይ ሥራዎች ግንዛቤ መፍጠሪያ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

399

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዛሬ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተጀምሯል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) መርሃ ግብሩን ዛሬ ረፋድ ሀዋሳ ላይ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ደግሞ በርዕሳነ መሥተዳድሮች፣ ከንቲባዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ነበር ያስጀመሩት፡፡ የችግኝ ተከላው በአማራ ክልልም በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ ተክለ ደብ ቀበሌ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ መርሃ ግብሩን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ናቸው ያስጀመሩት፡፡

በዚህ ክረምት በኢትዮጵያ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ 1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር ጌታቸው እንግዳየሁ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ በአብዛኛዎቹ የክልሉ አካባቢዎች በቂ ዝናብ አልጣለም፤ በመሆኑም ዛሬ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ የተከናወነው መስኖ ገብ የፍራፍሬ ልማት ባለባቸው አካባቢዎች ነው፡፡

ችግኝ ለመትከል በቂ የአፈር እርጥበት እና በቂ ዝናብ ሊኖር እንደሚገባ ያስገነዘቡት ዳይሬክተሩ የዛሬው አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዋነኛ ዓላማም የዓለም የአካባቢ ቀንን አስቦ ለመዋልና ዋናው የመትከያ ጊዜ እስኪደርስ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ ማሳሰብና ማስገንዘብ ነው፡፡

በክረምቱ ለተከላ አሰቸጋሪ በሚሆንባቸው፣ ለችግኝ ጽድቀቱ በማይመቹ፣ የበልግ ዝናብ አጥጋቢ በሆነባቸው (ከ20 እስከ 30 ሴንቲ ሜትር የአፈር እርጠበት ባለባቸው) አካባቢዎች እና ውርጭ በሆኑ የሰሜን እና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የሰሜን ሸዋ ዞኖች ቀደም ብሎ የተከላ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው ክረምት በአማራ ክልል ከሚተከሉት 1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ችግኞች መካከል 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የሚሆኑት የደን ቀሪዎቹ ደግሞ ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚሆኑ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል ባለፈው ክረምት ከተተከሉት ችግኞኝ መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

ፎቶ፡- በሰሎሞን ጥበቡ