“ዛሬ ላይ ሠላም አዲስ አደጋ ገጥሞታል፤ የዘንድሮው የዓለም የሠላም ቀን ትኩረቱን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አድርጓል” አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

171
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዓለም አቀፉ የሠላም ቀን በየዓመቱ መስከረም 10 ይከበራል፡፡ የዘንድሮው ዓለም አቀፉ የሠላም ቀን የትኩረት አቅጣጫውን ስለተፈጥሮ እየመከረ “የአየር ንብረት ለውጥ ለሠላም” በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ቀኑን አስመልከቶ ባወጣው መግለጫው የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልፅ የሆነ የሠላም እና ደኅንነት አደጋ ጥሏል ብሏል፡፡ በሰው ሰራሽ ግጭቶች ከመኖሪያ ቀየው ከሚፈናቀለው የዓለማችን ሕዝብ በሦስት እጥፍ በተፈጥሮ አደጋ የሚፈናቀለው ሕዝብ በልጧል፡፡ ምግብ፣ መጠለያ፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃ እና የአየር እጥረት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ያጋጠማቸው ሕዝቦች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

በዓለም ላይ በርካታ ዜጎች በተለያዩ የተፈጥሮ አዳጋዎች የሚኖሩበትን ቀየ ለመልቀቅ ተገድደዋል፡፡ ይህ የአየር ንብረት ለውጥ አዳጋ በየትኛውም አህጉር ባሉ ሁሉም ሀገራት ላይ የተከሰተ ቢሆንም የታዳጊ ሀገራት ዜጎችን ግን ባልፈጠሩት ስህተት የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ተነስቷል፡፡

‹‹ሠላም ዛሬ ላይ የተለየ አደጋ ገጥሞታል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በደኅንነት፣ በሕይወት እና በኑሮ ላይ አደጋ ደቅኗል፤ ለዚያም ነው የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሠላም ቀን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የተፈለገው›› ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተባበሩት መንግስት ድርጅት አባል ሀገራት በ2015 (እ.አ.አ) ፓሪስ ላይ የተፈራረሙትን ዘላቂ የልማት ግቦች ተፈፃሚ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‹‹ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ከተጋረጠባት አደጋ ነፃ በመሆን ሠላም የምታገኘው መንግሥታት ተጨባጭ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው›› ያሉት ዋና ጸሐፊው “ተፈጥሮ ለድርድር አትቀርብም” ብለው በ2050 ከካርቦን ልቀት ነፃ የሆነ ከባቢ ለመፍጠር እስከ 2020 ትኩረት በተሰጣቸው የአረንጓዴ ልማት ግቦች ላይ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ አሁን ላይ ካሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ያን ያክል ሲቀነቀንለት ባይሰማም ችግሩ የለም ማለት ግን አይደለም›› ያሉት በአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደን እና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ አወቀ ይታይ መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩርት እንዳልሰጡ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ልማት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው›› ያሉት አቶ አወቀ ልማቱ ግን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ተፅዕኖ የማያሳድር መሆኑን ማረጋገጥና ለትግበራውም ቅን መሆንን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹የተፈጥሮ ሚዛን የሚዛባባቸውን ሁኔታዎች በኢትዮጵያ እያስተዋል ነው፡፡ ችግሩ ሳይከፋ እና ስር ሳይሰድ እርምጃ ያስፈልጋል፤ ለዚህም ባለሀብቶች፣ ወጣቶች፣ ማኅበራዊ አንቂዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና ማኅበረሰቡ የየድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል›› ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here