“ዘፈን መታሰሪያ ድሮ እንዳልነበረ ፣ ወልቃይት ጠገዴ ያኮራኛል ጎንደር ሲዘፈን አደረ”

0
142

“ዘፈን መታሰሪያ ድሮ እንዳልነበረ
ወልቃይት ጠገዴ ያኮራኛል ጎንደር ሲዘፈን አደረ”
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ነፃነትን የሚተካው ነፃነት ብቻ ነው። እንኳንስ በግፍ የተወሰደ ማንነት ያለ አግባብ
የተወሰደች ዶሮም ታስቆጫለች። ታሳምማለች፣ ስለ ነፃነት የጮኹ ድምፆች፣ ስለ ነፃነት የታገሉ እጆች፣ ስለ ነፃነት የተራመዱ
እግሮች፣ ስለ ነፃነት የሰሙ ጀሮዎች፣ ስለ ነፃነት የተመለከቱ ዓይኖች ብዙዎች ነበሩ። ስለ ማንነት መሞት፣ ስለ ማንነት
መንገላታት፣ ስለ ማንነት መሰደድ።
መነሻዬ ከነገሥታቱ ሀገር፣ ከጥበቧ ከተማ፣ ከአርባራቱ ደብር መገኛ ጎንደር ነው። ታሪክ የዘከራቸው፣ ቅዱስ መንፈስ ያደረባቸው፣
ፍቅር የከተመባቸው ናቸው። በገነት ተራራ ግርማ፣ በጃን ተከል ዋርካ ጥላ፣ በፋሲል ግንብ ሞገስ፣ በአርባ አራት ታቦታት ቅዱስ
መንፈስ ከምትኖረው ጎንደር ከተማ ከትሜ ነበር ያደርኩት። ጎንደር ኢትዮጵያዊነት ይሰበክባታል፣ በኢትዮጵያዊነት ይኖርባታል። ስለ
ኢትዮጵያ ብዙ ነገር ተሰርቶባታል። በጎንደር አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ነፃነት፣ አሸናፊነት፣ ታላቅነት፣ አርቆ አሳቢነትና ጀግንነት አለ።
አዳሬ መልካም ነው።
የጨለማ ካባ ከምድር ላይ ሲገፈፍ፣ ብርሃን በተራው ምድርን ሊያደምቃት ሲወነጨፍ ከተኛሁበት ነቃሁ። ደስ የሚል ንጋት።
መዳረሻየን ወደ በረሃው ለማድረግ አስቢያለሁ። ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራን ለመቃኘት ጓጉቻለሁ። ጀንበር ስትሞቅ፣ ዝምታን
መርጣ ያደረችው ጎንደር ስትደመቅ በጎንደር ሰሜናዊ አቅጣጫ ወጥቼ ጉዞዬን ጀመርኩ። ጥቂት እንደተጓዝኩ የዳባት፣ የደባርቅ፣
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክና ሊማሊሞ መሄጃን መንገድን ወደ ቀኝ ትቼ ሰሜን ምዕራቡን መንገድ ይዤ ጉዞዬን ቀጠልኩ።
መንገዱ የአርማጭሆን ምድር እያቆራረጠ፣ ጠገዴን እያስቃኘ፣ ወልቃይት ጠገዴን እያሳዬ፣ ሰቲት ሑመራን አቋርጦ ተከዜን
የሚያሻግር ነው። የአርማጭሆ ኮረብቶች በአሻገር ሲታዩ ልብን ይሰርቃሉ። ቀልብን ይሰበስባሉ። አረንጓዴ ካባውን ያልተነጠቀው
መልከዓ ምድር ማራኪ ውበትን ተጎናፅፏል። በግራና በቀኝ እንደ ቤተመንግሥት እልፍኝ አስከልካዮች የተሰደሩት ኮረብቶችን
እየቃኘሁ ከአርማጭሆ የላይኛው ክፍል ወደታችኛው ወረድኩ።
ዝቅ እያሉ በሄዱ ቁጥር ወበቅ እየበዛ ይሄዳል። የሚጋረፍ ሞቃት አየር ይመጣል። አርማጭሆን ሲወርዱ በመንገዱ በስተቀኝ
በኩል ኢትዮጵያን ድንጋይ ላይ ይመለከቷታል። በጥበበኛ አናፂ የታነፀች የምትመስለው ድንጋይ የኢትዮጵያን ካርታ ታሳያለች።
የታደለ ምድር ድንጋዩ ኢትዮጵያን ቀርፆ ይዟል። ሰውም በኢትዮጵያ ፍቅር ተይዟል። እየተገረምኩ ጉዟችን ቀጠለ። ከተራራው
እየወረዱ በሄዱ ቁጥር መልክዓ ምድሩ ውበቱ እየጨመረ ይሄዳል።
ሁልጊዜም በጥንቃቄ የሚኖረው የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ንቃቱ፣ ፍጥነቱ፣ አለባበሱና አረማመዱ ልብ ይሰርቃል። በየመንገድ ዳሩ
የተሠሩ የበረሃ መንደሮችን እያቆራረጥን ሳንጃን አልፈን ወደፊት ገሰገስን። በረሃው እየተጋረፈ ነው። ጉዟችን ቀጥሏል። የበረሃ
መንደሮችን አቆራርጠን ሶሮቃ ከተማ ደረሰን። በሶሮቃ ከተማ መውጫ አካባቢ በስተ ግራ በኩል እርጎዬ፣ አዲስ ዓለምና
አብርሃጅራ የሚወስደውን መንገድ ያያሉ።
የእኔ ጉዞ ግን ወደዳንሻ ነበርና በስስት ተመልክቸው ወደፊት ገሰገስን። ሶሮቃ ከተማን እንዳለፉ ማንነታቸውን ተነጥቀው የኖሩ
ዜጎችን ማግኜት ይጀምራሉ። አሸባሪው ትህነግ ያለማንነታቸው ማንነት ሰጥቶ፣ መስመር ሰርቶ በጭቆና የኖሩ ዜጎች ናቸው።
ጉዟችን ቀጥሏል። ከወራት በፊት በዚያ ምድር ላይ የተካሄደውን የሕግ ማስከበርና የወያኔን ትቢት እያስታወስኩ ከነፍን።
ደማቋ ዳንሻ ከተማ ደርሰናል። ሙቀትና የሰው ድምቀት በከተማዋ ነግሷል። በመንገዱ ዳር በቆሙት አረንጓዴ ዛፎች ተቀምጠው
የሚጨዋወቱ ሰዎች ብዙ ናቸው። የተዘናጋ ሰው አይታይም። ሁሉም ጥንቁቅና ንቁ ነው። የበረሃውን ሙቀት ተቀበለን። የሰው
ፍቅርና ንቃት ደግሞ ሙቀቱን አስረሳን። አጄብ ነው። ዳንሻን አይቶ የማይገረም አይኖርም።
በዳንሻ የነበሩንን ሥራዎች እንጨርስ ዘንድ ጀንበርን በዳንሻ ከተማ ልናጠልቃት፣ ሌሊቱንም በዚያው ልናሳልፍ ተስማምተናል።
ያሰብነውን ፈፀምን። ጀንበር ጠለቀች። ብርሃን ለጨለማ እጅ ሰጠች። ዳንሻ ግን በድምቀቷ ቀጠለች። በምሽትም የምትደምቀዋን
ዳንሻን በቀስታ ቃኘኋት፣ ነፃነት ጠምቷቸው፣ ፍትሕ ተነፍጓቸው፣ ማንነታቸው ተወስዶባቸው ዓመታትን በትካዜ ያሳለፉት የወልቃይት
ሰዎች ደስታ ላይ ናቸው።
ዘፈን ምረጡ፣ በተመረጠላችሁ ልብስ አጊጡ የሚል የለም። ያ ዘመን አልፏል። እንደ ጨለማ ተገፏል። እንደ እንቦይ ፍሬ ረግፏል።
እንደ ጥላ አልፏል። በባሕል ማጌጥ፣ በሚስማማ መጨፈርና መደሰት ተጀምሯል። በአሸባሪው ትህነግ “ውጉዝ ከማርዮስ”
ተብለው የነበሩ የአማርኛ ዘፈኖች በከተማዋ ዳር እስከዳር ከፍ ብለው ይሰማሉ። ቤቶች በደስታና በፍቅር ደምቀዋል። አጄብ ነው።
ነፃነት ሲመለስ፣ ፍቅር ሲነግሥ ደስታውን በምን ይገልፁታል። ከተማዋ በደስታ ታመሰች።
ከተከዜ መለስ በሰፈሩት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ነዋሪዎች የግፍ ማዕበል ፈሷል። የጭካኔ ጥግ ደርሷል። የወልቃይት
ሰዎች የተወሰደባቸው ከንብረት፣ ከቤትና መሬት ሁሉ ይልቃል። የተወሰደባቸው ማንነት ነውና። ማንነት የተፈጠሩበት፣ የወረሱት፣
የሚኖሩት፣ የሚያከብሩት፣ የሚጠብቁት ከደምና ከአጥንት ጋር የተዋሐደ እንጂ ሲፈልጉ የሚያወልቁት ሲሻ የሚያጠልቁት
አይደለም። ማንነት በይሁንታ የሚሰጥ ስጦታም አይደለም። በግፍ የሚጭኑትም አይደለም። ማንነት ረቂቅ ነው።
የወልቃይት ሰዎች ግን ማንነት ተሰጥቷቸው፣ ያለኩት ማንነት ተሰፍቶላቸው። የእነርሱ ተወልቆባቸው የኖሩ ናቸው። ደስታቸው
ሲሹት የነበረውን በማግኜታቸው ነው። በሰው ደስታ መደሰት ሰውነት ነውና ደስታቸው ደስ ይላል። በዳንሻ የምሽት ድምቀት
ስደመም አምሽቼ ወደ ማደሪያዬ አቀናሁ። ሙቀቱ መጋረፉን አላቆመም። ዳንሻ እንደደመቀች ማደሪያዬ ተዘጋች። ነብሴም
በእንቅልፍ አረፈች። ጠዋትን እንዳይ አደራ የሰጠሁት ፈጣሪ አደራው ሳያጓድል ብርሃን አሳየኝ። እኔም አመሰገንኩት።
ደማቋ ዳንሻ በጠዋትም መድመቅ ጀምራለች። ጉዟችን ይቀጥላል። ዳንሻን ተሰናበትናት። የዳንሻን ሰሜን ምሥራቅ ንፍቅ ይዘን
ወደፊት ገሰገስን። የወልቃይት ጠገዴ ውብ ምድር ያማልላል። በበረኻው ውስጥ ሲጓዙ አልፎ አልፎ የመኖሪያ ቤቶች ይታያሉ።
በመልካዓ ምድሩ መደመሜ አላቆመም። አጀብ ያሰኛል። ልብን ይፈትናል።
በዚያ ምድር በእግር ለማቆራረጥ ወንድነት ይጠይቃል። የአካባቢው ነዋሪዎች ግን በነፃነት ይንቀሳቀሱበታል። ያለ ስጋት
ይኖሩበታል።
“ሰዎቹ ቀጭን ልባቸው ዳንዴ፣
የእነ አጅሮች ሀገር ወልቃይት ጠገዴ” የተባለላቸውም ለዚህ ነው።
በሰንሰለታማ ተራራዎች መካካል የተሠራውን መንገድ አቆራርጠን፣ ትንንሽ መንደሮችን አልፈን ወደ ወፍ አርግፍ ከተማ አቀናን።
በመልካሙ ምድር፣ በደጉ ሕዝብ ላይ ወያኔ ግፍ አድርሷል። የግፍ ዘመን አልፎ መልካም ዘመን መጥቷልና የመከራው ጥላ የተነሳ
ይመስላል። ጉዟችን ቀጥሏል። ሰንሰለታማ ተራራዎችን አቆራርጠን ወፍ አርግፍ ከተማ ከተምን። ወፍ አርግፍ ሽር ጉድ ላይ ናት።
የነፃነቱ ነጋሪት እየተጎሰመ፣ ጥዑመ ዜማ እየተዜመ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ እየተውለበለበ ከተማዋ ደምቃለች። ማደሪያችን
ወርፍ አርግፍ ሆኗል። በዚህች ከተማ የጭንቅ ዘመን ታልፎባታል። ማንነት ተገፎ በቀል ተሰብኮባታል። ነፃነት ተረግጦባታል።
ዘመን አልፎ ነፃነት ታውጆባታል። ማንነት ተመልሶባታል። ጀንበር ጠለቀች። ብርሃን እጅ ሰጠች።
የጀንበርን መጥለቅ ተከትለው የወፍ አርግፍ ጎዳናዎች እየደመቁ መጡ። ሀገርኛ የለበሱ ጎበዛዝትና ወይዛዝርት፣ በጎዳናው እየዞሩ
ይጨፍሩ ጀመር። ማንነት ሲመለስ፣ ታሪክ ሲታደስ፣ የደስታ ዘመን ሲደርስ ጭፈራው ደራ።
“አንቺ ያገሬ ልጅ ሽር በይ ባክሽ፣
እኔም ደስ ይበለኝ ሰዎቹም ይዩሽ” እየተባለ ይዘፈናል። ይጨፈራል። ጭፈራቸው ቀልብ ይሰርቃል። ዜማቸውና የሚደረድሯቸው
ስንኞች በከፋ ዘመን ውስጥ እንዳለፉ ያመላክታሉ። ጨፈራው ደርቷል። ጎዳናዎቹ በደስታ ተመሉ። ደስታ የራቃቸው ወይዛዝርትና
ጎበዛዝት በደስታ ከፍ አሉ። ዘፈን ሲመረጥባቸው፣ የአማርኛ ሙዚቃ ናፍቋቸው የነበሩ ጎዳናዎች ጠገቡት። ወጣላቸው።
ወይዛዝርቱና ጎበዛዝቱ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል የአንበሳ ደቦል በደስታ ዘለሉ። የታፈነው ደስታቸውን ያለ ከልካይ ለቀቁት።
“ሽር ብላ ደግሞ በጎንደር
ኮራ ብላ ደግሞ በጎንደር
እንዴት ብዬ ልደር” የጎንደርኛ የሙዚቃ ስልት ምሽቱን አደመቀው። የጎዳናው ጭፈራ ሲያልቅ በጋራ ወደ ሚዘፈንበት ቤት ገቡ።
በከተማዋ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ላደረጉ ሁሉ የምስጋና ድግስ ተደግሷልና በዋዜማ ነበር ይህ ሁሉ ደስታ። በአሸባሪው ትህነግ
ዘመን አማርኛ የሚዘፍኑ ከአማርኛም ወልቃይት ጠገዴን የሚያነሱ ሙዚቃዎች ፈፅመው የተከለከሉ ነበሩ። ያን ሲያደርግ የተገኘ
ሁሉ ይታሠራል፣ ይገረፋል። እንደ ጥፋተኛ ተቆጥሮ ይንገላታል። ጊዜ ደጉ ያነሳውን ጥሎ የጣለውን አነሳና ዘመን ተቀየረ።
“ዘፈን መታሰሪያ ድሮ እንዳልነበረ
ወልቃይት ጠገዴ ያኮራኛል ጎንደር ሲዘፈን አደረ” እንደ ወንጀል የተቆጠሩ ዘፈኖች በከተማዋ ነግሠው አደሩ።
ለመናገር ብቻ ሳይሆን ለመደሰትም ገደብ ተጥሎባቸው የነበሩ ዜጎች ያለ ገደብ ተደሰቱ። ያለ ስጋት ሀሴት አደረጉ። ሌሊቱ በደስታ
ተመላ። የፍቅር ማዕበል በከተማዋ ወረደ።
“ድል ያለ ድል ነው ወገን ተሰብሰብ
ዳግም ሆነናል አንድ ቤተሰብ” እንዳለ ከያኒው የአንድ ቤተሰብ ልጆች ደስታቸውን አንድ ላይ ገለፁ። ከተማዋ በደስታ ዘለለች።
ነፃነት ተመለሰች፣ ፍቅር ዳግም መጣች።
“ክብሩ ሲመለስ ማንነቱ የሰው፣
ታናሽ ታላቁን ደስታ አስለቀሰው” ደስታ ሆነ። በደስታቸው ተገረምኩ። ምን አይነት ዘመን ውስጥ እንደነበሩ አሰብኩ። በደስታቸው
እንኳንስ ሰው ጎዳናው ሳይገረም አልቀረም። ደስታችሁ የእውነት ነውና፡፡ ሰላም።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here