“ዘመን ባንክ ራሱን በቴክኖሎጂ እያዘመነ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ አሻራውን እያስቀመጠ ነው” የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጀ ዘበነ

23

ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዋና ሥራ አስፈጻሚው ባንኩ በመጭው ቅዳሜ የሚያስመርቀውን ባለ 36 ወለል እና 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን ዘመናዊ ሕንፃ ምረቃ እና ባንኩ አሁን የደረሰበትን ደረጃ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በመግለጫቸው የተገነባው ሕንፃ ጥሩ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ያረፈበት፣ ለደንበኞች ምቹ አገልግሎት ለመሥጠት ታስቦ የተገነባ ደረጃውን የጠበቀ ሕንፃ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ለከተማዋም መልካም ውበትን የሚያላብስ ነው ብለዋል።

ባንኩ ሀብታቸውን በአግባቡ ከሚጠቀሙ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንደኾነ ገልጸዋል።አሁን ላይ ባንኩ 40 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት፣ 35 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ እና 31 ቢሊዮን ብር ለብድር አገልግሎት ማዋሉን ገልጸዋል።

የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ኤርሚያስ እሸቱ ባንኩ ዘመኑን የዋጀ አግልግሎት ለደንበኞች እየሰጠ እንደኾነ ገልጸዋል። ዲፖዚት የሚቀበሉ ኤቲ ኤም ካርዶችንም ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያደረገ ነው ብለዋል። በ87 ሚሊዮን ብር እና በአንድ ቅርንጫፍ ሥራ የጀመረው ባንኩ አሁን ላይ ካፒታሉ አምስት ቢሊዮን ብር መድረሱን እና በቅርቡ 101ኛ ቅርጫፉን መክፈቱን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!