ከንግስና በፊት ካሳ ኃይሉ፣ በጦር ስማቸው መይሳው ካሳ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ እና በንግስና ስማቸው ደግሞ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ይባላሉ። ሥራዎቻቸውን ዘመን ከማይሽራቸው ጥቂት ጥበበኛ መሪዎች ውስጥ አንዱ ናቸው ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ።
ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት ተወልደው እና የዘመነ መሳፍንት ሥሪት ሆነው ሳለ ለዘመነ መሳፍንት ማርከሻ የሆኑ፣ ከትንሽ ተነስተው ከዙፋን የደረሱ፣ ከኖሩበት ዘመን የገዘፈ ታሪክና ጀብድን የከወኑ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል። ከአስተሳሰባቸው ከዘመኑ የቀደመ እንደነበረ የሚናገሩም አልጠፉም። ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት የየአካባቢው ነገስታት እንደ ቅርጫ ስጋ ተበጣጥሳ ልታልቅ ባለችበት ዘመን ነው መፍትሄ የሆኑት፡፡ ያንን አስከፊ ጨለማ ገፈው እና አራግፈው የአንድነት የብርሃን ችቦ የለኮሱ መሪ ናቸው፤ ዓፄ ተዎድሮስ፡፡
ከኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራባዊ ጫፍ ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ አባታቸው በሚያስተዳድሩት ቋራ ጥር 6/ 1811 ዓ.ም ነበር ይህችን ምድር የተቀላቀሉት፡፡ ካሳ ኃይሉ አጥንት እና ደም ተቆጥሮ ለሹመት ያውም ለዘውድ በሚታጭባት ሃገር የረባ የንግስና ዝናና ስም ከሌላቸው ቤተሰቦች ተወልደው ‹‹ኢትዮጵያን አንድ ያደርጋሉ›› ብሎ ያሰባቸው አልነበረም። ዳሩ የነፍስያ ጥሪያቸው መሪነት ነበር እና መሪ ለመሆን የወሰደባቸው ውጣ ውረድ ከባድ እና ፈታኝ አንዳንዴም የማይታመን አይነት ቢሆንም ፈፅሞ መሪ ከመሆን ያገዳቸው አልነበረም።
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አባታቸውን በሞት ካጡ በኋላ ከእናታቸው እና ከዘመዶቻቸው ጋር የተለያየ የህይዎት ምዕራፍን አሳልፈዋል። የጀግንነት እና የጥሩ መሪ ሰብዕናን ግን በሽፍትነት ዘመናቸው ጫካ ውስጥ እንደተማሩ እና እንዳጎለበቱ በርካቶች ይስማማሉ። አስተሳሰባቸው ተራማጅ፣ ውሳኔያቸው ላቅ ያለ እና ስልጣኔን ናፋቂ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም ‹‹ክፍለ ዘመኑን ቀድመው የተወለዱ›› ይባላሉ።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1947 እስከ 1983 ዓ.ም ›› በሚለው መጽሐፋቸው ንጉሱን ‹‹ብልጭልጭ ነገር የማይስባቸው እና የወታደሮቻቸውን ኑሮ የሚጋሩ መሪ›› ሲሉ ይገልጿቸዋል። ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የተወለዱበትም ሆነ ወደ መንበረ ንግስና የመጡበት ወቅት ሃገራቸው በበርካታ ፖለቲካዊ ችግሮች እግር ከወርች የታሰረችበት ነበር፤ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተፅዕኖዎች የበዙበት እና ሁሉም የየአካባቢው ነገስታት ራስ ገዝ አስተዳደር ለመመስረት የሚፍጨረጨሩበት ወቅት ላይ መምጣታቸው በቀላሉ ሃሳባቸው እውን፣ ፍላጎታቸው ገቢር እንዳይሆን አድርጓቸዋል።
ያም ሆኖ ግን ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት እና ወታደር ያላት ሃገር ለመመስረት ጥረት አድርገዋል። ስልጣኔን ናፋቂ፣ የምዕራባዊያኑን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አነፍናፊ፣ የነበሩት ዓፄው የኋላ ኋላ የአስተሳሰብ ምጥቀታቸው ወግ አጥባቂ ከሆነው ሕዝብ ጋር አልጣጣም ብሎ ውድቀታቸውን አፈጠነው። እንዲያውም የማታ ማታ የዘመነ ንግስናቸው ፍፃሜ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በ1860 ዓ.ም ድል አድራጊው የእንግሊዝ ጦር አዛዥ ለነበረው ሮበርት ናፒየር ‹‹ያገሬ ሰው ገብር እና ሥርዓት ግባ ብየ ብለው እምቢ ብሎ ተጣላኝ። እናንተ ግን በስርዓት በተገዛ ሰው አሸነፋችሁኝ፤›› ሲሉ የፃፉት የስንብት ደብዳቤ ወቅቱን እና ማንነታቸውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ለዚህም ይመስላል ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ ‹‹የዘመናዊ ስልጣኔ ሃሳብ የገባው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉስ ነበር›› ማለታቸው።
እኒህ ጀግና የሃገር መሪ፣ አርቆ አሳቢ እና የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ንጉስ ዛሬ ከተወለዱ 201 ዓመት ሆናቸው። እኛም ስለ እርሳቸው አዲስ ሀሳብ ባንነግራችሁም ልደታቸውን ዘክረን እና አክብረን “እንኳንም ተወልደው አለፉ!” አልናቸው።
በታዘብ አራጋው