“ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ፣ የነጻነታችን ምልክት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ተምሳሌት፣ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ደም የተገነባ የድል ቀን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

0
43
“ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ፣ የነጻነታችን ምልክት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ተምሳሌት፣ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ደም የተገነባ የድል ቀን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር
ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) 125ኛው የዓድዋ ድል በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡ በክበረ በዓሉ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አባት አርበኞችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በበዓል አከባበሩ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን አፍሪካዊ ወንድሞቻችንን ነጻ ለማውጣት የበኩላችንን አስተዋጾኦ ያደርግንበት ቀን በመሆኑ ሁሌም በዓለም አደባባይ ስናከብረው እንኖራለን” ብለዋል ርእሰ መሥተዳደሩ፡፡
የዘንድሮው የዓድዋ በዓል አከባበር ልዩ የሚያደረገው የምንጊዜም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይም የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆነው የትህነግ ጁንታ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ክብረ በዓልንና የሕግ ማስከበር ዘመቻችን በሁለት ነገሮች ይመሳሰሉ ያሉት ርእስ መሥተዳደሩ የመጀመሪያው በሁለቱም ጊዜ እብሪተኝነት የተሞላ ግፍ ተፈጽሟል ነው ያሉት፡፡ እብሪተኝነትም ለውድቀት ይዳርጋል፤ ጁንታው በኢትዮጵያ ሕዝቦችና በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጽመው እብሪትም ለውድቀት ዳርጎታል ነው ያሉት፡፡
ሌላኛው “ትጥቅ እስከ አፍንጫ ታጥቂያለሁና ድል አስመዘግባለሁ ማለት እንደማይቻል ግንዛቤ የተወሰደበት ነው” ብለዋል፡፡ ማንም ኀይል እስከ አፍንጫው መሣሪያ ቢታጠቅ የሚዋጋ እና የማሸነፍ ሥነ ልቦና ከሌለው ማሸነፍ እንደማይችል ግንዛቤ የተወሰደበት ነው ብለዋል፡፡
ትህነግ የአማራ ሕዝብን አዋርዶ አንገት ለማስደፋት በአጭር ሠዓት ውስጥ ጎንደርንና ባሕር ዳርን ለመቆጣጠር ያሰበው እብሪት ከሽፏል ብለዋል፡፡
የአሸነፍነውም እውነትን ስለያዝንና ለነጻነታችን ስለታገልን ነው፣ልበ ሙሉዎች ስለነብርንም ነው ብለዋል፡፡
“አውሮፓውያን ኢትዮጵያ እንድትንበረከክ ፍላጎት ነበራቸው” ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ በኋላም ወደ ዲፕሎማሲ የመጡት ድል ስለተመዘገበ ነው ብለዋል፡፡ ድሉም ዓለም ስለ አፍሪካ እንዲያስብ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ድሉ አፍሪካውያን ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕግ ለማስከበር መንግሥት የወሰደውን ርምጃ ሃብት ያላቸው ሀገሮች በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን ከሳሽ ሆነው መቅረባቸውም ተቀባይነት የለውም፡፡ እውነቱ ግን በማይካድራ የተጨፈጨፉት ወገኖች፤ በመከላከያ ኀይላችን ላይ የደረሰው ግፍ ነው ብለዋል፡፡
ሕግ የማስከበር ዘመቻውን በድል አጠናቀናል ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ ከዚህ በኋላ ማንም ኃይል የአማራን ሕዝብ አንገት የማስደፋት ሙከራ ቢያደርግ ራሳችንን የመከላከል ተመጣጣኝ ርምጃ እንወስዳለን፤ ወልቃይት ጠገዴ የተደረገው ውጊያ ማንነትን ለማረጋገጥ እንጂ መሬት ለመውረር አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹በመሰረቱ እኛ ከዚህ በኋላ ነፃ ወጥተናል›› ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ ነጻ የወጣ ሕዝብ ደግሞ ወደ ባርነት መልሶ አይገባም፤ እንቅፋት አንድ ጊዜ እንጂ ሁለት ጊዜ አይመታም ብለዋል፡፡
በተለያዩ መንገድ አንድነትን ለመሸርር የሚጥሩ ኀይሎችን መታገል እንደሚስፈልግም ተናግረዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ በጎጥና በመንደር አይከፋፈልም፤ ከፋፋዮች የጁንታው ተላላኪዎች ናቸው ያሉት ርእስ መሥተዳደሩ ሁሉም ጉዳይ ከአማራ ሕዝብ በታች ስለሆነ ለሕዝቡ የማይከፈል መስዋዕትነት የለም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here