‘‘ዓመቱን ሙሉ ዝናብ አይለየንም፤ በሥራችን ልክ ጥቅም አግኝናል፡፡’’ በአሳግርት ወረዳ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተጠቃሚ የሆነ ወጣት

132

‘‘ኅብረተሰቡን የሥራው ባለቤት ማድርግ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡’’ የአሳግርት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት

‘‘በተሠራው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡’’

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ በሰንሰለታማ ተራሮች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተሠራላት፣ በተለያዩ ደኖች ያሸበረቀች፤ ቦታ ላይ ተገኘቶ ለሚመለከተት ሰው እጅግ የሚያማልል ማራኪ ናት፡፡ ነዋሪዎችም በጋ ላይ ጠንክረው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሠርተዋል፤ ክረምት ላይ ደግሞ በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ማጠናከራቸውን ከቦታው ተገኝተን ተመለክተናል፡፡

ወይዘሮ ሙላታ አበራ አሳግርት ወረዳ አጎዶ ቀበሌ ይኖራሉ፡፡ የእርሳቸው መሬት በብዛት ተራራማ እንደሆነ ነግረውናል፤ ተመልክተናልም፡፡ ተራራማ በመሆኑም ከዚህ በፊት (የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሳይሠራለት) አርሰው ለመጠቀም አስቸጋሪ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ለዓመታት ሳይጠቀሙት እንደኖሩ ገልፀዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ በተራራው ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በሚገባ ሠርተዋል፡፡ በሥነ ሕይወታዊ ዘዴም አጠናክረዋል፡፡ በተራራው ላይ ጌሾ እና ቡና በብዛት ተክለዋል፤ ከዚህም በዓመት ከ20 ሺህ ብር ያላነሰ ገቢ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡ በሚያገኙትም ገቢ ደግሞ ቤታቸውን በአግባቡ እየመሩ ልጆችን ያለ ችግር ማስተማር እንደቻሉ ነግረውናል፡፡

አቶ መርሻ ግርማ ደግሞ አሳግርት ወረዳ ጥደሽ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ነው፡፡ ‘‘ተራሮችን ተንተርሰው የተጋደሙ ደንጋዮች ብቻ ይታዩበት የነበረውን አካባቢ በዛፍ ማለምለም ችለናል፤ ዓመቱን ሙሉ ዝናብ አይለየንም፤ በሥራችን ልክ ጥቅም አግኝናል’’ ብሏል በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ያመጡትን አካባቢያዊ ለውጥ ሲናገር፡፡

አቶ መርሻ ከ15 ወጣቶች ጋር ተደራጅቶ በደን ልማት ሥራ በመሰማራት በማኅበሩ 160 ሺህ ብር ማገኘታቸውን ገልጿል፡፡ በቁጥቋጦ ብቻ ተሸፍኖ የነበረውን ተራራ በማልማት ደግሞ ለሰው ልጆች ንጹሕ አየር እንዲገኝ ከማስቻል በተጨማሪ ልዩ ልዩ የዱር እንስሳት በአካባቢው እንዲጠለሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቋል፡፡

የአሳግርት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በላይነህ ማሞ በወረዳው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ‘‘ኅብረተሰቡን የሥራው ባለቤት ማድርግ ደግሞ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን አድርጎታል’’ ብለዋል፡፡ በወረዳው የደን ሽፋን 16 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ደግሞ በአንድ ቀን በዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡ ‘‘የተዘጋጁ ችግኞች በ34 ተፋሰሶች ይተከላሉ’’ ያሉት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ግብርናው በወረዳው 70 በመቶ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር እየተሠራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ መሠረት ኃይሌ ደግሞ ዘንድሮ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚተከሉ በቆጠራ የተረጋገጡ 232 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ባበለፉት ዓመታት 23 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመተከል ዕቅድ ተይዞ ከዕቅድ በላይ 24 ሺህ 768 ቦታ በደን መሸፈኑን ነው ወይዘሮ መሠረት የተናገሩት፡፡ የመጽደቅ ምጣኔ ደግሞ 80 በመቶ ማድረስ መቻሉን ነው ያመለከቱት፡፡

በተሠራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዜጎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቡና፣ ጌሾ፣ ጤና አዳም እና ልዩ ልዩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች እንዲሸፈኑ በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው