“ውስን የኾነውን የበጀት ሀብት ይበልጥ ጥቅም በሚሠጡ ተግባራት ላይ በማዋል የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል” የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ

30

ባሕርዳር : ግንቦት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው የዓመቱን በጀት በአግባቡ እየተጠቀመበት እንደኾነ አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የበጀት ዝግጅት እና አሥተዳዳር ዳይሬክተር ሙሉሰው አይቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት ለበጀት ዓመቱ ያቀደውን 95 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል አስፈላጊው ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በጀቱ ለሦስቱ የአሥተዳዳር እርከኖች የሚከፋፈል ሲኾን እንደ ድርሻቸው እንደሚወስዱም አቶ ሙሉሰው አስታውሰዋል፡፡

በጀቱ ለክልል ቢሮዎች 31 በመቶ፣ ቀበሌን ጨምሮ ለወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች 58 በመቶ የሚወስዱ ሲኾን 10 ነጥብ 38 በመቶ ለጋራ ችግሮች በተጠባባቂነት እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙሉሰው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለደመወዝ ከተመደበው 62 በመቶ፣ ለሥራ ማስኬጃ ከተመደበው 67 በመቶ እና ለካፒታል ፕሮጀክቶች በክልል 18 በመቶ በወረዳ እና በከተማ አሥተዳደሮች 37 በመቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል፡፡

በክልል ለሚገነቡ 858 ፕሮጀክቶች 18 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የተበጀተ ቢኾንም በተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የዋጋ ጭማሪ የተነሳ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም 18 በመቶ ብቻ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

አቶ መሉሰው በዋጋ ንረት ምክንያት ሥራ ያቋረጡ ተቋራጮች ወደ ሥራ እንዲገቡ ክልሉ 60 በመቶ የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉን አንስተዋል፡፡ ሀገሪቱ ላይ እየታየ ያለው 66 በመቶ የዋጋ ግሽበት ሥራዎች እንዲቋረጡ እና አዳዲስ ጨረታዎች እንዲወጡ ማስገደዱን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የፍኖተሠላም እና የደብረብርሃን ጠቅላላ ሆስፒታሎች ውለታቸው ተቋርጦ አዲስ ጨረታ የወጣባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የካፒታል በጀት ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣ ቢኾንም የግንባታ እቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መናር ምክንያት ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ሙሉሰው ተቆጣጣሪ አካላት የፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተሻለ እንዲኾን ሂደቱን መገምገም እና ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸውም ነው ያስረዱት፡፡ አማካሪዎች ሥራው በቀረበበት ወቅት ተረክቦ የክፍያ ሠርተፊኬት በማዘጋጀት ለከፋይ መሥሪያ ቤቶች ማቅረብ፣ ከፋይ መሥሪያ ቤቶችም ክፍያውን በወቅቱ በመፈጸም ፕሮጀክቶች በወቅቱ የሚጠናቀቁበትን ኹኔታ ማማቻቸት ተገቢ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ክልሉ የሚባክን በጀት እንዳይኖር አሠራር ዘርግቷል ያሉት ዳይሬክተሩ በአሠራሩም የክልል ቢሮዎች በጀት ሊቃጠል ነው በሚል ሰበብ ከመጋቢት 30 በኋላ ለወረዳዎች እንዳይልኩ፣ ከሚያዝያ 30 በኋላ የበጀት ዝውውር እንዳይሠራ አሠራር መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ሒሳቡ ባለበት መደብ ላይ ኾኖ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እንዲሠሩ ቁጥጥር እና ክትትል እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በክልልም ኾነ በወረዳ በጀት የሚገዙ ቁሶች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲኾኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሠጥተው እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡

አቶ ሙሉሰው በጀት ውስን ሃብት እንደኾነ ገልጸው የበጀት ተጠቃሚ አካላት ይኽን ውስን የኾነ ሃብት ይበልጥ ጥቅም ለሚሠጡ ተግባራት በማዋል የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!