ወጣቶች የኢትዮጵያዊያን መጻኢ ዕጣ ፋንታ የተሳሰረ እና የማይለያይ መኾኑን በውል መገንዘብ እንዳለባቸው የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አዳም ፋራህ ተናገሩ።

41
ባሕር ዳር:መጋቢት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በባሕርዳር ከተማ ሲካሄድ በቆየው የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የስልጠና መድረክ ማጠናቀቂያ ዝግጅት ላይ ተገኝተው ለሰልጣኞች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል። ወጣቶች የኢትዮጵያዊያን መጻኢ ዕጣ ፋንታ የተሳሰረ እና የማይለያይ መኾኑን በውል በመገንዘብ ለሀገር አንድነት እና እድገት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ወጣቶች የወንድማማችነት ስሜትን የበለጠ ማዳበር፣ ሀሳብ ለሀሳብ መደማመጥ እና መተሳሰብ ያስፈልጋል ሲሉ አቶ አደም ገልጸዋል። ጫፍ እና ጫፍ ቁሞ የየራስን አካባቢያዊ ችግር ብቻ ከማንሳት ይልቅ ሌላው አካባቢ ያሉ ችግሮችንም መገንዘብ እና በትብብር ለመፍታት መጣር ግድ ይላል ሲሉም ተናግረዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች በማኅበረሰቦች መካከል ድልድይ በመኾን ለኢትዮጵያዊያን አብሮነት መጠናከር ሊሠሩ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል። በስልጠና ላይ ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ለራሳቸው እና ለሀገራቸው ለውጥ በሚኾን መልኩ ተርጉመው ሕዝብን እንዲያገለግሉም ለወጣቶች መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ አደም ስልጠናው የተሳካ እንዲኾን የአማራ ክልል ላደረገው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!