ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የአማራ ክልል ምክር አባላት በየደረጃው ከሕዝብ ጋር በነበራቸው ውይይት የያዟቸውን የሕዝብ ጥያቄዎች ለክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የምክር ቤት አባላቱ ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ያደረጓቸውን ውይይቶች አበረታች ብለውታል፡፡ የክልሉ ሕዝብ በየደረጃው ያነሳቸውን ጥያቄዎች በጥንቃቄ እና የሀገረ መንግሥት ምስረታውን በማያደናቅፍ መልኩ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ የሠላም እና የፀጥታ ስጋቶች ከክልሉ ውጭ በሚፈጠሩ ችግሮች የሚያገረሹ ናቸው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ የመጫረሻ ግባቸው የአማራን ሕዝብ በሰላም መንሳት የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት እንዳይመሰረት ለማድረግ ያግዛል ከሚል የተሳሳተ ስሌት የመነጩ ናቸው ብለዋል፡፡
የክልሉን ሕዝብ የኅልውና ሥጋቶችን እና ችግሮችን ለመፍታት የሀገሪቱን እና የክልሉን ነባራዊ ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ በሳል የትግል ስልት እየተከተሉ መኾኑን አንስተዋል፡፡
የአማራን ሕዝብ የመብት፣ የማንነት እና የወሰን ጉዳዮችን ለማስከበር ኢትዮጵያዊነት መሰባሰቢያ ጥላችን ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳደሩ “ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮቻችን ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግሥት ምስረታ ሥራችን ካለመጠናቀቁ የመነጩ ናቸው” ብለዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ጊዜያት ሥራዎች ይፈቱታል ብለን ስለምናምን የክልሉ መንግሥት የምክክር ኮሚሽኑን እያገዘ ነው ብለዋል፡፡
የዜጎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከአማራ ክልል አዲስ አበባ የተነሳው የተጓዦች ችግር ተገቢነት ያለው ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ክልከላው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በጣሰ መንገድ መፈጸሙ ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ ችግሩን ለመፍታት መንግሥታቸው ከሚመለከተው ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት ተከትሎ የሠላም ሥምምነት ላይ መድረሱ ተቀብሎ ለሠላም እየሠራ ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በትግራይ ኃይሎች በተያዙ ሁለት ወረዳዎች ለጊዜው የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል፡፡
የተነሱ የመልካም አሥተዳደር፣ የመሰረተ ልማት እና የመልማት ጥያቄዎችን ለመፍተት በቀጣይ ጊዜያት ከክልል ቢሮዎች ጋር እየተነጋገሩ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!