ወርልድ ቪዥን በአማራ ክልል በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተፈፃሚ የሚሆን ከ965 ሚሊዮን ብር በላይ የልማት ሥራዎች የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

0
54
ወርልድ ቪዥን በአማራ ክልል በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተፈፃሚ የሚሆን ከ965 ሚሊዮን ብር በላይ የልማት ሥራዎች የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች እና 13 ወረዳዎች በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተፈፃሚ የሚሆን ከ965 ሚሊየን ብር በላይ የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አሰፋ እሸቴ ወርልድ ቪዥን ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆኖ መቀጠሉን አውስተው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተጠናክሮ እደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
በአምስት ዓመቱ የስትራቴጅክ ዕቅድም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከ965 ሚሊየን 153 ሺህ ብር ወይም ከ24 ሚሊየን 217 ሺህ ዶላር በላይ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን አቅዷል ተብሏል፡፡
ጤና፣ ትምህርት፣ ውኃና ንጽኅና አጠባበቅ፣ ሴቶች፣ ህፃናት፣ የመስኖ ግንባታ እና የግብርና ልማት ሥራዎች የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አቶ አሰፋ ጠቁመዋል፡፡
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተወካይ ስቴፈን አንድሪው ኮርት ወርድ ቪዥን ላለፉት ዓመታ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተኮር የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አውስተው በህፃናት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ንፁህ ውኃ ግንባታ እና መሰል የልማት ሥራዎች ላይ አጋር ሆኖ ዘልቋል ብለዋል፡፡
የወርልድ ቪዥን ሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ስትራቴጅክ የልማት አጋር ቢሮ ኀላፊዎች ተገኝተው የስምምነት ሰነዱን ፈርመዋል፡፡ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ክልሉን በመወከል የተገኙት የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶክተር) ወርድ ቪዥን ኢትዮጵያ የክልሉ የዘመናት የልማት አጋር ሆኖ መዝለቁን አውስተው በቀጣይም ክልሉ ይህንን የልማት አጋርነት አጠናክሮ መቀጠል ይፈልጋል ብለዋል፡፡
የወርልድ ቪዥን ሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ የቀጣዮቹን አምስት ዓመታት ስትራቴጅክ እቅድ በጋራ የተገመገመ ነው ያሉት ዶክተር ጥላሁን ለተፈፃሚነቱ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡ ለቀጣዩ አምስት ዓመታት የልማት ሥራዎች ከፀደቀው 24 ሚሊየን 217 ሺህ 226 የአሜሪካን ዶላር ውስጥ 24 በመቶው በዋሽ መርሃ ግብር ለንፁህ መጠጥ ውኃ ግንባታ እና 22 በመቶው ለትምህርት ይውላል ተብሏል፡፡ 39 ብሎክ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎችም ይገነባሉ ትብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here