ወልቃይት ጠገዴ ለጠላት ምኅረት የላትም፡፡

0
157
ሁመራ፡ መስከረም 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ አማራ በእሳት ተፈትኖ የወጣ ሕዝብ ነው፡፡ በማኅበራዊ መስተጋብሩ ውስጣዊ አንድነቱን አጠናክሮ በመደራጀት ማንነቱን ለማስከበር ጠላቱን ለዓመታት ታግሏል፤ በጠላት ላይ ድል ያላስመዘገበበት አውደ ውጊያ የለም፡፡ ለዚህም ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በአሸባሪው ትህነግ ላይ ያደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ሕያው ምስክር ነው፡፡
ሻምበል ባሕታ መኩሪያ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብት ጠብቀው፣ እርፍ ጨብጠው ቢያድጉም የወጣትነት እድሜያቸውን ያሳለፉት ከአሸባሪው ትህነግ ጋር በመፋለም ነው፡፡ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ከቻለ ሀገርን እየበዘበዘ በጉልበት ለመግዛት፤ ካልሆነም በተዳከመች ኢትዮጵያ ላይ ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ወልቃይት ጠገዴን በጉልበት ከተቆጣጠረ በኋላ በኢትዮጵያዊ አቋም ስለማንነታቸው የትግሉን አቀበት ከተጋፈጡ የቁርጥ ቀን ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ከ1981 ዓ.ም ጀምረው ከወንድሞቻቸውና ሌሎች ታጋዮች ጋር ጫካ በመግባት የከፋኝ ቡድን መስርተው ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር ወራራውን በጽናት ታግለዋል፡፡ በትግላቸውም የቡድን እና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መማረክን ጨምሮ በአሸባሪው ትህነግ ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሰዋል፡፡
የሽምቅ እና የግንባር ፍልሚያውን መቋቋም ተስኖት ሽንፈት የተከናነበው አሸባሪ ቡድን በንጹሐን ላይ የበቀል ርምጃ ማድረስ ጀመረ፡፡ ወልቃይትን በጉልበት ባስተዳደረባቸው ዓመታት እሱ ከሳሽ፣ ራሱ ምስክር፣ ራሱ ዳኛ ሆኖ በርካታ ታጋዮችን ለእስርና ለስቃይ ሲዳርግ የብዙዎችን ደብዛም አጥፍቷል፡፡
ሻምበል ባሕታ ስለማንነታቸው ባደረጉት ትግል ብዙ ውጣውረዶችን አሳልፈዋል። ሊገድሏቸው ይፈልጓቸው ስለነበር ሀገር ጥሎ መሰደድን የመጨረሻ እጣ ፈንታቸው አድርገው ዘጠኝ ዓመታትን በሱዳን አሳልፈዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በግብታዊነት ለራሱ በሰጠው የተሳሳተ ግምት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ ክህደት ፈጽሞ በወገን ጦር ድባቅ እየተመታ ባለበት ጊዜ ሻምበል ባሕታ ሕዳር 11/2013 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡
አሁን በወልቃይት ጠገዴ ፍጹም ሰላም ሰፍኗል፤ ለዓመታት ተጨቁኖ የነበረው ሕዝብም ነጻነቱን እያጣጣመ ብዙዎች የሞቱለትን እና መስዋእትነት የከፈሉለትን ዓላማ ዳር ለማድረስ በከፍተኛ የጀግንነት ወኔ እየታገለ ነው፡፡ የመታገያ ሜዳውም ምቹ ነው፡፡ ሴት ወንድ ሳይሉ ጠላት ድጋሜ ፊቱን እንዳያዞር ከማድረግ ባለፈ ጠላትን እስከወዲያኛው ለማጥፋት ቁልፍ ቦታዎችን ዘግተዋል፡፡
በተለይ የቀድሞ ከፋኝ መሥራች አባላት ጠላት ዳግም ወደ ወልቃይት ጠገዴ ፊቱን ከመለሰ እንኳን ሕዝቡን የተጠለሉበትን ዛፍ ከማጥፋት ወደ ኋላ እንደማይል ስለሚያውቁ ሕዝቡን ደጀን በማድረግ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይል እና ፋኖ ጋር ተሰልፈዋል፡፡ የወገን ጦር አሰላለፍ ለውስጥ ባንዳም ሆነ ለውጪ ጠላት የሚንበረከክ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በደም እና በአጥንት የተገነባች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘናት ሰንደቅ ዓላማቸው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እና የሀገራቸውን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ተዋድቀዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ሀገርን እንደ ዳቦ ቆራርሰው ከሚሰጡ ባንዳዎች ጋር የሚደረገው ትግል የዚህ ታሪክ አካል ነው፡፡ እናም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ለማስቀጠል በሚችለው አግባብ መታገል አለበት ነው ያሉት፡፡
እንደ ሻምበል በሕታ ንግግር የኢትዮጵያ ስም ነገ እንዳይደበዝዝ ወጣቱ መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል፣ በመሰልጠን እና በመታጠቅ ሀገሩን ከውርደት መታደግ ይኖርበታል፣ ባለ ሀብቶችም ትግሉን በገንዘብ የመደገፍ እንቅስቃሴን እስከ ፍጻሜው ማጠናከር አለባቸው፡፡ አዛውንት እና የሃይማኖት አባቶች በጸሎት እንዲሁም ምሁራን ችግር ፈቺ የመትፍሔ ሐሳብ ማመንጨት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ግርማዋ ትመለሳለች፤ ሕዝቦቿም ፊታቸውን ወደ ልማት ያዞራሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ