ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!

0
204

ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አምስት ዓመታትን በምናብ ወደኋላ መጓዝ ከቻልን “ወልቃይት” ለመላው የአማራ ሕዝብ የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል፤ የአንድነታቸው ማህተም የሆነችበትን ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም እናገኛለን፡፡ ይህች ቀን የአንድ ሀገር ዜጎች ሰርግና ለቅሶን ያስተናገዱበት ዕለት ጭምር ነበረች፡፡

የባሕር ዳር ወጣቶች ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም በጎንደር የተለኮሰውን የነፃነት ትግል አቀጣጥለው “ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ሲሉ እስከሕይዎት መስዋእትነት እየከፈሉ ይወድቃሉ ይነሳሉ፡፡ እነነውር ጌጡ ደግሞ የአማራ ማንነት ጥያቄን አከርካሪ የሰበሩ መስሏቸው በበርሃዋ ገነት እና በተከዜ ወንዝ በራፍ በበቀለችው የአማራ ከተማ ሁመራ ላይ እነ ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በተገኙበት የብርጭቆ ፍብሪካ መሰረት ድንጋይ አስቀመጥን ሲሉ ተዘባበቱ፡፡

ፍትህ የናፈቃቸው፣ ነፃነት የጠማቸው እና ማንነታቸው እንዲከበር የሚሹ ድምጾች በሀገሪቱ በርካታ ቦታዎች ውስጥ ለውስጥ ቢሰሙም በአማራ ክልል አካባቢዎች ግን ነገርየው የከረረ ይመስል ነበር፡፡ እስከአፍንጫው የታጠቀን ኀይል ፊት ለፊት ያውም ደግሞ በባዶ እጅ ለመግጠም መቁረጥ ሁኔታውን “የዳዊት እና ጎዶሊያድ ፉክክር” አስመስሎታል፡፡

የአማራ ሕዝብ ትዕግስት መሟጠጡን ጎንደር ነጋሪት ጎስማ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ብታውጅም ተስፋ ያልቆረጡት አምባገነን ተስፋፊዎች የሞት ሽረት ትንቅንቅ ለማድረግ ግን አልሰነፉም ነበር፡፡

ባሕር ዳር ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም ጎዳናዎቿ በአመጽ ሰልፍ ሲናወጡ ያዩት ጡት ነካሾች ፍርሃት ሲያርዳቸው ባዶ እጃቸውን ለተቃውሞ በወጡ ወጣቶች ላይ ምህረት አልባ ሰይጣናዊ እጆቻቸውን አሳረፉባቸው፡፡ የዛች ውብ ከተማ ገዳናዎች በልጆቿ ደም ክፉኛ ጨቀዩ፡፡ ወጣቶች ስለጓደኞቻቸው፣ ወላጆች ስለልጆቻቸው እና ማኅበረሰቡ ስለወገኖቹ ደም ከፉኛ አነቡ፡፡

በጎማ ጭስ አመጽ አመድ የመሰለችው ባሕር ዳር ጸዳሏ ተገፎ ቀናትን በሐዘን ድባብ ውስጥ አሳለፈች፡፡ በዚች ዕለት በርካታ የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች “ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” እያሉ ራሳቸውን እስከወዲያኛው አሳልፈው ሰጡ፡፡

ያ መስዋእትነት እስከ ወርሃ መጋቢት 2010 ዓ.ም ድረስ ደመ ከልብ ቢመስልም ዛሬ ኢትዮጵያ ቀና ትል ዘንድ የተከፈለ ክቡር መስዋእትነት ነበር፡፡

ዛሬ የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች የሰማዕታቱን ገድል በበርሃዋ ገነት ለመዘከር የመጡ ወንድሞቻቸውን ከባሕር ዳር በክብር ሲቀበሉ “በልጆቻችን ደም ነፃ ወጣን” ሲሉ ተደመጡ፡፡ አንዳንዶቹ በስሜት፣ አንዳንዶቹ በስስት እና በአክብሮት አይኖቻቸው እምባ እንዳቀረሩ በተከዜ ዳር ፈርጥ ሁመራ ከተማ ተቃቅፈው ሲሳሳሙ ላየ “ዘር ከልጓም ይጠቅሳል” የሚለው የሀገሬው ሰው ብሂል ተብሲሩ ይገባዋል፡፡

“የወንድሞቻችን መስዋእትነት ከንቱ አልነበረም” የሚሉት የባሕር ዳር ወጣቶቹ ስለማንነት፣ ስለነፃነት እና ፍትህ ሲሉ የተሰው ወንድሞቻችን ጥያቄ ተመልሷል ይላሉ፡፡ “ያስመለስነው ማንነት እንጂ የነጠቅነው መሬት የለም” ያሉን ወጣቶቹ የአማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ዳግም ላይቀለበስ በወንድሞቻቸው ደም መመለሱንም ነግረውናል፡፡

ዛሬ ወደ ሁመራ ያቀኑትም ወቅቱ የሚጠይቀውን የሕልውና ትግል መደገፍ እና ለዳግም የነፃነት ፍልሚያ ከወገኖቻቸው ጎን መቆማቸውን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡

ነሐሴ 1/2013 ዓ.ም የባሕር ዳር ወጣቶች በሁመራ ችግኝ እየተከሉ አረም እየነቀሉ እንደሚያሳልፉ ነግረውናል፡፡

በታዘብ አራጋው -ከሁመራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m