ካሜሩን አዲስ አሰልጣኝ ቀጠረች፡፡

0
72

ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) ‹የማይበገሩት አንበሶች› በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀውን የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን እንዲያሰለጥኑ አዲስ ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡

አሰልጣኝ ቶኒ ኮሲሶ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን የካሜሩን የስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ኮሲሶ ብሔራዊ ቡድኑን ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያሰለጥኑ ከሳምንት በኋላ ሊገለጽ እንደሚችልም ተነግሯል፡፡

አዲሱ አሰልጣኝ በቀድሞው የካሜሩን የእግር ኳስ ተጫዋችና የ1988 (እ.አ.አ) የአፍሪካ ዋንጫ ባለድልና የሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ፍራንኮይስ ኦማም ቢይክ ረዳት አሰልጣኝነት እንደሚታገዙም ተሰምቷል፡፡

አሰልጣኙ ካሜሩንን በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ እንደሚመሩና ለ2022 የኳታሩ የዓለም ዋንጫ እንደሚያደርሱ ይጠበቃል፡፡ አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድንን ሲያሰለጥኑ የመጀመሪያቸው ሲሆን በአውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ ቡድኖችን ማሰልጠናቸው ታውቋል፡፡ በ20 ዓመታት የአሰልጣኝነት ዘመናቸው በአራት ሀገራት የሚገኙ 14 ቡድኖችን ማሰልጠናቸው ነው የተገለጸው፡፡

በ11 ዓመታት የእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመናቸው ደግሞ ለፖርቱጋሎቹ ብራጋ፣ ቪዝላ፣ ሪዮፔል እና ፖርቶ ተጫውተዋል፤ ከፖርቶ ጋርም ሁለት ዋንጫዎችን አንስተዋል፡፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ለፖርቱጋል መሰለፍ የቻሉት፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ

በአብርሃም በዕውቀት