ከ140 በላይ በሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ላይ የተጫኑ ተተኳሾችን መያዙን የሃገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ፡፡

0
1244
ከ140 በላይ በሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ላይ የተጫኑ ተተኳሾችን መያዙን የሃገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) ህገ ወጡ፣ ወራሪው እና ተስፋፊው የትህነግ ቡድን ለከፈተው ጦርነት የሎጀስቲክ ማዕከል አድርጎ ሊጠቀምበት ያሰበውን ቦታ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ተቆጣጥሮታል፡፡ በሎጀስቲክ ማዕከሉ የቡድንና የግል መሳሪያዎች፣ የነዳጅ ቦቲዎች፣ ታንኮች፣ ሮኬቶች፣ የአየር መቃዎሚያ እና ታላላቅ የድርጅት እና የግል ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ፅንፈኛው ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከወር በፊት ጦርነት ሲያውጅ ተስፋ ካደረጋቸው መካከል በግዛት ዘመኑ ለዕኩይ ተልዕኮው ካካበታቸው የጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ ከሰሜን ዕዝ የዘረፋቸው የጦር መሳሪያዎች ቀዳሚዎቹ ነበሩ፡፡ በሂደት የከፈተው ጦርነት ቀቢፀ ተስፋ እንደነበር የተረዳው ትህነግ የጦርነቱን አካሂድ ለመቀየር መሞከሩን የሚያመላክቱ አሻራዎችም ታይተዋል፡፡ ከዚህ መካከል አንዱም ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ከማዕከሉ አሽሽቶ በአንድ አካባቢ ማከማቸቱ ነበር፡፡
በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ አካባቢ ባሉ የድንበር ቦታዎች ከፍተኛ ምሽግ ቆፍሮ ሲዋጋ የነበረው ትህነግ የመከላከያ ሰራዊትን ጥቃት መቋቋም ሲሳነው አፈገፈገ፡፡ የህገ ወጡን ቡድን ዱካ እየተከተለ የሚያሳድደው ሰራዊትም ትህነግ ከእይታ ውጭ ይሆናል ያለችውን ከተከዜ መለስ ያለውን የጭላ ወረዳ በርሃማ ቀበሌዎች ሳይቀር ተቆጣጠረ፡፡
የ11ኛ ክፍለ ጦር 3ኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ያሲን ኑርየ ትህነግ ይህንን አካባቢ መከላከያ ሃይሉ ይደርስበታል ብሎ እንዳላሰበ ይናገራሉ፡፡ እንደ አዛዡ ገለፃ በዚህ አካባቢ ከመከላከያ የተዘረፉ ተሽከርካሪዎች፣ የድርጅት ከባድ መኪኖች፣ የሲቪል መኪኖች እና ከ140 በላይ በሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ላይ የተጫኑ የከባድ እና ቀላል ጦር መሳሪያ ተተኳሾችን በመከላከያ እጅ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከከባድ ተሽከርካሪዎቹ መካከል 36ቱ የመስፍን ኢንዳስትሪያል ድርጅት እና ሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡
የነዳጅ ቦቲዎች፣ መድፍ፣ አየር መቃዎሚያ፣ ሞርተር፣ ዲሽቃ፣ ፀረ ሰውና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጆች እና የቡድን እና የግል የጦር መሳሪያዎች አፈር በተቀቡ እና ቅጠል በለበሱ ተሽከርካሪዎች ላይ በበርሃው ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ የተበተነው ሃብት በጥንቃቄ እየተሰበሰበ እንደሆነ የገለፁት ኮሎኔል ያሲን ቀጣዩ ተልዕኮም ወታደራዊ ሚሊተሪ አውልቀው ሲቪል በመልበስ በአርሶ አደሩ ቀየ የተሰገሰጉ ተፈላጊዎችን መያዥ ነው ብለዋል፡፡
ይወጡባቸዋል ተብለው የታሰቡ ድንበሮች መዘጋታቸውን እና አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም ኮሎኔል ያሲን ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከየጭላ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ