“ከ139 የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድም ሴት የፓርቲ መሪ የለም:” ወይዘሮ ሳባ ገብረ መድህን- የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር

0
128

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱት 139 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንድም የሴት መሪ እንደሌለ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረ መድህን አስታወቁ።

ዋና ዳይሬክተሯ ይህንን ያሉት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ታስቦ ተናንት በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ነው:: በስልጠናና ውይይቱ 70 የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎችና ተወካዮች እንደተሳተፉ ታውቋል፡፡

የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የተናገሩት ወይዘሮ ሳባ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱት 139 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንድም የሴት መሪ ያለመኖሩን አንስተዋል፡፡

በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ንቁ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሴቶች በፖለቲካ ላይ ያላቸውን ዝቅተኛ ተሳትፎ ማሻሻል እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካይና የቦርድ አባል ወይዘሮ ብዙወርቅ ከተተ በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እጅግ ያነሰ እንደሆነና ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባው መሆኑን መናገራቸውን አዲስ ዘመን ዘግቧል፡፡

አዲስ የተሻሻለው የምርጫ አዋጅ ለሴቶች የተሻለ ዕድል የሚከፍት መሆኑን፣ ሴቶችም በተፈጠረው እድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here