“ከፍ ያለው የዓድዋ ዘመን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ዛሬም መደገም አለበት፡፡” የሥነ ልቦና ባለሙያው ሙሉዓዳም ታምሩ

21

ባሕርዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍ ያለው የዓድዋ ዘመን ሥነ ልቦና ዛሬም መደገም እንዳለበት የሥነ ልቦና ባለሙያው ሙሉዓዳም ታምሩ ተናገሩ፡፡

የሥነ ልቦና ባለሙያው ሙሉዓዳም ታምሩ ዓድዋ በዓለም ታሪክ ውስጥ ገዝፈው ከሚነገሩ ታሪኮች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል፡፡ የሰው ልጅ ማየት ከሚፈልጋቸውና ማድረግ ከሚሻቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ አሸናፊነት ነው፡፡ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ማሸነፍ አይታወቅም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግን ለዘመናት ለነጮች የውስጥ ህመም ኾኖ የዘለቀውን የዓድዋ ጦርነት አሸነፈች፡፡

ነፃነቷን አውጃ ለዘመናትም ዘለቀች፡፡ አይበገሬነት እና ነፃነት ህልማቸው ለኾነው መሪያቸው ሕዝቦች ታዘዙ፡፡ እናት ሀገራቸው በጠላት እንዳትወረር በንቁ አእምሮ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ቋንቋ፣ የመሬት አቀማማጥ፣ የቦታ ርቀት ሳያግዳቸው፣ ሳይከፋፍላቸው ኢትዮጵያዊያን ስለሀገራቸው ክብር፤ ስለ ራሳቸው ነፃነት በጋራ ተሰለፉ፡፡

የሀገር ፍቅርን በተላበሰ ሥነ ልቦና የእናት ሀገራቸውን አንድነት ለማስጠበቅ አውሮፓውያን ከታጠቁት ዘመናዊ መሣሪያ የገዘፈ ሥነ ልቦናን ተላብሰው ኢትዮጵያዊያን በጋራ ኾነው ጠላትን ተፋለሙ፡፡ ለዚህ መነሻው ደግሞ የንጉሡ ጥንካሬ ነበር፡፡ ንጉሡ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ በብስለታቸው የተመሰከረላቸው በመኾናቸው ቀድመው የሚመጣውን ችግር ተረዱ ፣አወቁ፡፡

“ጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከትተህ ጠብቀኝ አሉት” ታማኙ ንጉሥ ፣ለታማኙ ሕዝብ፡፡ ሕዝቡ ለልጁ፣ ለሚስቱ፣ ለእናቱ እና ለሀገሩ ሲል እንዲዋጋ ጥሪ አስተላለፉ፡፡ ርህራሄን፣ ጽናትን፣ አንድነትን፣ ይቅርታን እና ማስተማል የተሞላበት ጊዜን መሠረት ያደረገው አዋጅ ንጉሡ በሥነ ልቦና መዘጋጀታቸውን ማሳያ ነበር። ሕዝቡም ንጉሡን አምኖ ለጦርነት የተሠለፈበት መንገድ የሕዝቡን የሥነ ልቦና ከፍታ የሚያሣይ ነው ብለዋል አቶ ሙሉ ዓዳም ታምሩ፡፡

መጭውን ድል ቀድመው የተረጎሙት አጼ ምኒልክ አዋጃቸውን በአጭሩ አስተላለፉ፡፡ በሥራቸው የሚገኙ የጦር አበጋዞች፣ ደጃዝማቾች የቦታ ርቀት ሳይበግራቸው ሁሉም ወደ አንድ መምጣታቸው የሥነ ልቦና ከፍታን ያሳያል ብለዋል፡፡ የሀገርን ፍቅር ከሁሉም ያስበለጡት ሹማምንቶች ያሳዩት ተሳትፎ በዘመኑ የነበረውን የሥነ ልቦና ደረጃ ማሳያ ነው ፡፡

ሀገሪቱ ወደ ጦርነት እንደገባች ያወቁት የቁርጥ ቀን ደጀኖቹ ኢትዮጵያዊያን የትኛውም አይነት ልዩነት ሳይገድባቸው፤ በየሠፈሩ የቀሩ ሰዎች አካባቢያቸውን ነቅተው በመቆጣጠር፤ ሌባውን እና አጭበርባሪውን ማሳደዳቸው የነበረውን የሥነ ልቦና ከፍታ ያሳያል ብለዋል፡፡

ዓድዋ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዓድዋ ምድር ላይ ሲካሄድ አጼ ምኒልክ የሚያሸንፈኝ የለም ሲሉ ፣ሕዝቡም እኔም ለሀገሬ ዋጋ እከፍላሉ ብሎ ልጁን፣ሚስቱን እና ንብረቱን ለሀገሩ አደራ ጥሎ ሆ ብሎ ሲነሳ የሕዝቡ ሥነ ልቦና አስደናቂ ነበር ነው ያሉት፡፡

አጼ ምኒልክ የክተት አዋጅ ሲያውጁ የሚመሩትን ሕዝብ ሥነ ልቦና ጠንቅቀው የሚያውቁ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡ ለዚህም ማሳያው በሕዝብ መካከል ምንም ያክል ቁርሾ ቢኖር በሀገር ጉዳይ ላይ ግን ሁሉም የሚነሳበትን ጥበብ ተጠቅመዋል ፡፡ ይኽውም በክተት አዋጃቸው “ስንቅህን ባህያህ አመልህን በጉያህ” በማለት ለሀገር ክብር፤ነጻነት እና አንድነት ሁሉም በነቂስ ወጥቶ እንዲዋጋ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ሕዝቡም የተነገረውን አዋጅ በመገንዘብ የአሸናፊነትን ሥነ ልቦና በመያዝ ተዋግቶ አሸንፏል፡፡

ተመሳሳይ ዓላማ የነበረው ሕዝቡ ወደ ጦርነት ሲሄዱ አንዱ ካንዱ ይበልጣል እገሌ ከእገሌ ይቅደም የተባለ ነገር አልነበረም፡፡ አጼ ምኒልክ ሕዝባቸውን ለጦርነት በአዋጅ ሲጠሩት እንደሚያሸንፉ እምነት ነበራቸው፡፡ አንድን ነገር ለመፈጸም ደግሞ የሥነ ልቦና ዝግጅት ትልቁን ቦታ ይይዛል ብለዋል፡፡

ካሕናቱ ታቦት ተሸክመው፣ አዝማሪዎቹ መኳንንቱን እያወደሱ፣ ሴቶች ስንቅ እያዘጋጁ፣ ልብስ እያጠቡ፣ ምግቡ እና መጠጡ ለወራት ሳይጎድል መጓዛቸው ኅብረትን፣ አንድነትን፣ ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆምን እና የሥነ ልቦና ከፍታን የሚያሳይ መኾኑን መመልከት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የዓላማ ጽናት እናሸንፋለን፣ የሚያሸንፈን የለም የሚለውን መተማመን አምጥቶ ለውጤት አብቅቷቸዋል ብለዋል፡፡ በጉዞ ወቅት ከአድዋ በፊት የነበሩ ታሪኮችን እያወሱ ይነጋጋሩም ነበር፡፡

ሌላው በጦርነቱ ወቅት ከኋላ ደጀን የነበረው ጦር ከፊቱ ያለው ጀግና ሲወድቅ ወደ ፊት ተራመደ እንጂ ወደ ኋላ አልሸሸም፤ ረጅሙ ጉዞ ብዙ አስተምሮን አልፏል፡፡ መደማመጥን፣መተጋገዝን አብሮነትን ለሀገር ክብር በአንድ መሰለፍን አሳይቷል ዓድዋ፡፡

ጣሊያን በሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ላይ የነበራትን መፈራት በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም ህልም የነበራት ሀገር ብትኾንም አልተሳካላትም፡፡ የገጠሙት ቀድመው በሥነ ልቦና የተዘጋጁትን አጼ ምኒልክን ስለነበር ነው፡፡ ንጉሡ ለሕዝቦቻቸው ያሳዩት ርህራሄ እና የነበራቸው እምነት ለድል አብቅቷቸዋል፡፡

ንጉሡ አዋጅ ሲያስነግሩ ሕዝቡ እምቢ አልቀበልም አላላም፤ ሕዝቡ ንጉሡን ያምናቸዋል፤ ያከብራቸዋል፤ ይታዘዛቸዋል፤ ከመታዘዝም አልፎ ጥሪያቸውን ተቀብሎ ለሀገሩ ሲል ሕይወታቸውን አሳልፈው በመስጠት መስዋዕት ኾነዋል፡፡

ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካም ነፃነትን አውጇል፡፡ጥቁር ማሸነፍ እንደሚችል፣ ነጭ በጥቁር ጠንካራ ምት የተንበረከከበት ብቸኛው የውጊያ አውድ ዓድዋ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ታላቅ ባለውለታ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን እናት እንድትባል ያስቻላት አድዋ እንደኾነም ማወቅ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይኾናል ተብሎ የማይታሰበውን ጣሊያንን ድል አድርጋ ያሳየች፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ግዞት በቃን፣ ባርነት ይቁም ብለው እንዲነሱ ምክንያት እና ምሳሌ የኾነች ሀገር ናት፡፡ ምነው ቢሉ የሥነ ልቦና ደረጃቸው ምጡቅ በኾኑት በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ትመራ ስለነበር ነው፡፡ ጣሊያኖች ይህንን መገመት ባለመቻላቸው የሽንፈትን ጽዋ ሳይወዱ ተግተዋል፡፡ ዛሬም ከቀደምት አባቶቻችን ወኔ፣ ጥንካሬ፣ ማስተዋል እና የሀገር ፍቅርን መማር ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ሀገር ጠባቂነትን እና ሀገር ወዳድነት ይዘን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ሥነ ልቦና ከመማር ይገኛል፤ የትናንትን እርካብ ጨብጦ፤ ነገን በእጅ ለማድረግ የታላላቆቻችንን አርዓያነት መከተል ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የነገ ተስፋችን እንዲለመልም የትናንት ማንነታችን የዛሬ ኑባሬያችን ሊፈተሸ ይገባል ነው ያሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው።

ዓድዋ የትናንት ታሪካችን ቢኾንም ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ በዚያ ዘመን በነበረው ልክ ማስረዳት ማሳወቅ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የዓድዋ ድል ሀገር ወርሬ እንቁላል አስገብሬ እኖራለሁ ብሎ በትዕቢት የመጣው የጣሊያን ሠራዊት ተሸንፎ በየገደሉ፣ በየተራራው፣ በየወንዙ ወድቆ የአሞራ እና የአራዊት እራት ኾኖ የቀረበት በመኾኑ ታሪኩ በዛ ዘመን ልክ ለትውልዱ መድረስ አለበት ብለዋል፡፡
ያሁን ዘመን ልጅ መቼ ይሠማል ሳይኾን መባል ያለበት የቅድመ አያቶቻቸውን ታሪክ ሊነገራቸው ይገባል፤ይሕ ታሪክ በዓለም አደባባይ በኩራት ብትናገረው ማንነትህን ቀድሞ ይገልጣል፤ የነበርክበትን ከፍታ ያመለክታል በሚል ሊነገራቸው ይገባል ብለዋል የሥነ ልቦናው ባለሙያ፡፡

ታሪክን ለነገ ማሻገር ካልተቻለ ምንም እንደሌለን፣ እንዳልነበረን እንዳልሠራን እና አሸናፊ እንዳልኾንን ሊቆጥሩን ይችላሉ እና ይህ ስህተት መታረም አለበት ብለዋል፡፡

ባዶነት እንዳይሠማን ማንነታችንን እንዳንለቅ አባቶች ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ እኛ ማን ነን ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የምናገኝ መኾን አለበት ብለዋል፡፡ ጀግናን እንደጀግና ማወቅና ማክበር ያስፈልጋል፡፡ እምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ የፈጸሙት ታሪክ ኢትዮጵያን በትክክል ይገልጻታል ብለዋል፡፡ “ዓድዋ” በተራራ ላይ በተቀመጠ መቅረዝ ላይ የሚበራ ሁሉም የሚያየው፣ የሚያደንቅው ድል ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ጥበብን አብዝተን የምንወድ፣ ነጻነትን የምንመርጥ ሕዝቦች መኾናችን ከዓድዋ በፊት የነበሩ ታሪኮቻችን ይናገራሉ ያሉት አቶ ሙሉአዳም ዓለም የሚያውቀውን እውነት እኛ አለማወቅ ጥፋት ነው ብለዋል፡፡

በጦርነቱ የተሳተፉ የኢትዮጵያ ልጆች በመካከላቸው የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የቦታ አቀማመጥ፣ የቀለም፣ የዘር እና ሌሎችም ልዩነቶች ነበሯቸው፡፡ እነዚህን ልዩነቶች ግን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ለሀገራቸው በነበራቸው ፍቅር፣ ለንጉሣቸው በሰጡት ክብር፣ ለቤተሰቦቻቸው በሰጡት ሕይወት በጋራ ተሠልፈዋል፡፡

ታላቁንና ሀገር የመሠከረለትን የነጮችን አንገት ያስደፋው የዓድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት አስገኝቷል፡፡ ዛሬም የሀገር ፍቅር፣ ኅብረት፣ ሰላም ወዳድ፣ አንድነትን አክባሪ፣ እኔ ለወንድሜ ስል ቀድሜ ልሙት የሚል ትውልድ እንዲፈጠር ሁሉም መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

የራስን ታሪክ ሳይኾን ሌሎች የሠሩትን ቀላል ታሪክ በማድነቅ የራስን እንዲተው ለማድረግ የሚጥሩ ኀይሎች መለየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዓድዋ ድል ያለን ግንዛቤ ማደግ የጠቢብነታችን ማሳያ እና መለኪያም ነው ብለዋል፡፡ ታሪካችንን እያየንበት ያለው ሁኔታ ስህተት የኾነ ዕርዮተ ዓለም ለችግር እንዳያጋልጠን መጠንቀቅ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ልጆች ከንጉሡ እስከ ሕዝቡ ድረስ የነበራቸው አንድነት አንዱ ለአንዱ የሠጠውን ግምት መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ በክተት አዋጅ የተጠራው ሕዝብ ንጉሡን ተከትሎ ሲዘምት አሸንፎ እንደሚመለስ ያውቅ ነበር፡፡
አቶ ሙሉአዳም የትናንት ታሪኮቻችን ዛሬ ለደረስንባቸው የወረዱ አስተሳሰቦች መገንቢያ መኾን እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡

ዛሬም ነገም ለአንድነት፣ ለፍቅርና ለኅብረት ቅድሚያ መሥጠት አለብን ብለዋል፡፡የእኛ ታሪክ ልምድ የተቀመረበት አንድነትን እና ፍቅር የታየበት የኢትዮጵያውያን ልማድ ነው ብለዋል፡፡

ከፍ ያለው የዓድዋ ዘመን ሥነ ልቦና ዛሬም ድህነትን በመዋጋት መደገም አለበት ብለዋል አቶ ሙሉአዳም፡፡ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ውስጥ ጎልታ የምትታወቀው ሕዝቦቿ በድል አድራጊነት፣ በሥነ ልቦናቸው ከፍ ያሉ በመኾናቸውን ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!