“ከግጭት ጋር ተያይዞ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር ፣ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ሊተባበር ይገባል” ጤና ሚኒስቴር

54
ባሕር ዳር:መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ከግጭት ጋር ተያይዞ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር ፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጤና ሚኒስቴር ከግጭት፣ከድርቅና ከወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ምላሽ መስጠትንና በግጭት ምክንያት የተጎዱ ጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ ከአጋርና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ አካሒዷል።
በውይይቱ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት ከግጭት ጋር ተያያይዞ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር ፣ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ክልሎች ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም ሁሉም አጋር አካላት በቅንጅት መረባረብ አለበት።
በድርቅ የተጎዱን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ እንደ ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ ወባ፣ ሊሽማኒያሲስ እና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ቢሆንም አሁንም ትልቅ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
አሁን ያለው ተደራራቢ የኅብረተሰብ ጤና ችግር ሰፊ ምላሽ እንደሚያስፈልገው የገለጹት ዶክተር ሊያ በአንዳንድ አካባቢዎች አጋር አካላት በቂ ድጋፍ የሚሰጡ ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በሚፈለገው መጠን እንደሌሉ ጠቁመዋል።
May be an image of 7 people, people standing, people sitting and suit
ይህንን ችግር ለመፍታት የሚመጡ ግብዓቶችንና ድጋፎች በአግባቡ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የሚደርሱበትንና ክትትል የሚደረግበትን የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው በሃገሪቱ ከግጭቱ ጋር ተያይዞም ሆነ በድርቅ ምክንያት ለሚከሰቱ የሥነ-ምግብና የጤና ችግሮች ምላሽ ለመስጠት በቅድመ ማስጠንቀቂ የቅኝት የመረጃ ሥርዓት አማካኝነት የማጣራት ሥራ እየተሰራ ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
“አሁን ካለው ዘርፈ ብዙ ችግር ጋር ተያይዞ አጋር አካላት ከጤና ሚኒስቴርና በየደረጃው ካሉ የጤና መዋቅሮች ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና የሚወጡበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን” ብለዋል፡፡
በቅንጅታዊ ሥራዎችም የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግና በፍትሃዊ የሃብት አጠቃቀምና ስርጭት ምላሽ አሰጣጡን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በመድረኩ እንደተገለጸው በቀጣይ የአራት ወር የተዘጋጀው የጋራ ዕቅድ በሃገር አቀፍ ደረጃ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለሚመራው ካውንስል ቀርቦ ከሌሎች ሴክተሮች ጋር በመቀናጀት በሃገር አቀፍ ደረጃ በረዥም ጊዜ ችግሮቹ እንዳይከሰቱ፤ ሲከሰቱም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችልም ተጠቁሟል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሠ፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ፣ የአጋር ድርጅቶች የሥራ ኀላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!