ባሕር ዳር:መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ዓለሙ አለምነህ በቋሪት ወረዳ አሸቲ ሌባገደል ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ዓለሙ በአካባቢው መንገድ ባለመኖሩ በርካታ ነፍሰ ጡር ሴቶች ጤና ጣቢያ ሳይደርሱ ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡ አካባቢው ተራራ በመኾኑ ኹሉም ነገር በሰው ጉልበት ነው የሚንቀሳቀስ ነው ያሉት፡፡
አካባቢው በብዛት ጤፍ ፣በቆሎ፣ ሽምብራ እና ገብስ በብዛት ያመርታል ብለዋል፡፡ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ ደግሞ እንሰሳትን ለማጓጓዣነት ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜ ይወስዳል የበርካታ ሰዎችን ጉልበት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ “አሁን መንገዱ በተጠረገበት አካባቢ ጋሪ እየገባ ድካማችንን ቀንሶልናል” ብለዋል አርሶ አደሩ፡፡ የታመሙ እና ችግር የገጠማቸው ሰዎች በሞተር ወደ ሕክምና ቦታም እየደረሱ ስለመኾናቸው አስረድተዋል፡፡ አርሶ አደር ዓለሙ መንገዱ ያለውን ጥቅም በመረዳታቸው የመንገድ ግንባታውን ለመደገፍም ቁርጠኛ ስለመኾናቸው ነግረውናል፡፡
ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባንቴ አላምረው የመንገዱ መገንባት የአካባቢው ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ነበር ብለዋል፡፡ መንገዱ ብዙ ጥቅም አለው ያሉት አርሶ አደር ባንቴ ከሌላ ወረዳ ጋር እንገናኛለን፣ ምርታችንንም ለገበያ እናቀርባለን ነው ያሉት፡፡ መንገዱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅም ብርቱ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የቋሪት ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ መዝገቡ ውቤ የመንገዱ መገንባት የወረዳዋን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል፡፡ የመንገዱ ግንባታ በመቋረጡ ማኅበረሰቡ ጥያቄ እያነሳ ነበር ድጋሚ በመጀመሩ ደስተኛ ነው ብለዋል፡፡ ድጋፍም እያደረገ ስለመኾኑ አስረድተዋል፡፡ የማሽን እጥረት መኖር ሥራውን ቢያጓትተውም ባላቸው ማሽን እየሠሩ ነው፡፡ እኛም ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፈንታሁን መንግሥቴ የሕዝቡን የመንገድ ጥያቄ ለመመለስ ዞኑ ደረጃ በደረጃ እየሠራ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ የገበዘ ማርያም-ሃሙስ ወንዝ-ሰከላ መንገድ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንጻር በተያዘለት ጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ ባይቻልም አሁን ባለው ሥራ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን አንስተዋል፡፡ ለመንገዱ መጓተት ምክንያቱ የገጠመው ሀገራዊ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ፈንታሁን በቀጣይ በተሻለ መንገድ እንዲጠናቀቅ ዞኑ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡
በአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የገበዘማርያም ሃሙስ ወንዝ ሰከላ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ኀላፊ ኢንጅነር ኃይለየሱስ የማነ መንገዱ በሁለት አቅጣጫ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ መንገዱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንገዱ 104 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 20 ሚሊዮን 630 ሺህ 630 ብር ተበጅቶለታል፤ በ6 ዓመት ይጠናቀቃልም ተብሎ ታቅዷል ነው ያሉት፡፡
ኢንጅነር ኃይለየሱስ መንገዱ አሁን 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ጠረጋ፣ አፈር የመደልደል ሥራ እና የምንጣሮ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡
የሲሚንቶ እና የነዳጅ ዋጋ መናር እንዲኹም በሚፈለገው መጠን አለመገኘት ፣ የሥራ ማሽን አለመኖር እና የግል ባለሃብቶች ገብተው ለመሥራት ፈቃደኛ አለመኾን ለሥራው ትልቅ ማነቆ ኾነው መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!