ከደሳሳ ጎጆ እስከ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ምንጭነት።

0
150

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 06/2012ዓ.ም (አብመድ) ምሁራን ዘመናችን የጨለማ ዘመን፣ የድንጋይ ዘመን፣ የነሃስና የብረት ዘመን ብለው ይከፍሉታል፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ ታዲያ የሰው ልጅ ዘመኑን የሚመጥን የመገናኛ መንገድ ነበረው፡፡ ይህ ዘመንም ዘመኑን የዋጀ የራሱ የሆኑ የመገናኛ ዘዴዎች አሉት፡፡ ዓለም በመረጃ እጥረት ምክንያት ብዙ ነገር አጥታለች፡፡ መራመድ በሚገባት ልክም እንዳትሄድ ሆና እንደነበር ይነገራል፡፡ በለተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት በመረጃ እጦት አሁን ድረስ ማጥ ውስጥ ናቸው፡፡ ሀገራቸው እንዴት ውላ እንዳደረች፣ ዘመኑን እንዴት መዋጀት እንዳለባቸውና ሌሎች ጉዳዮችን የማየትና የመስማት አድል ብዙም የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያም በዚሁ የመረጃ እጦት ብዙ ነገሮችን አጥታለች፡፡ የመረጃ ማጣት፣ መዘግየትና ትክክለኛ አለመሆን ሀገሪቷን ሲፈትናት ኖሯል፤ እየፈተናትም ነው፡፡

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነው፤ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ የስልጣን መንበሩን እሰኪይዝ በነበረው የሽግግር ጊዜ ነው የተወጠነው፡፡ የኢሕአዴግን መንበረ ስልጣን አያያዝና በዘመኑ የነበሩ መልካም ተግባራትና ህፀፆችን በድፈረት ዘግቧል፡፡ ለአብነት በ1989 ዓ.ም በአማራ ክልል የተደረገውን የመሬት ድልድል ሁኔታ በተመለከተ ዘግቧል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት በኃላፊነት ከባሩድ ስር ሆኖ ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ዓለም የማያውቋቸውን ክዋኔዎች፣ የማኅበረሰብ ክፍሎችና ታሪካዊ ቦታዎች ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ አውጥቶ አሳይቷል፡፡ ግዛት ቀርቶ ክልል ሲመጣ በክልል ደረጃ የሚወዳደረው የለም፣ ቀዳሚ ተመራጭና ተአማኒ ነው፡፡ ድርጅቱ እንደሌሎች የዓለም መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ሁሉ ባማረ ቤት፣ በተሟላ የሰው ኃይልና ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ የመመስረት ዕድል አልነበረውም፡፡ ይልቁንስ የድንጋይ ወንበር፣ የጉልበት ጠረጴዛ ይዞ በአንዲት ትንሽ ጎጆ ውስጥ ነበር የተቋቋመ፡፡ ጋዜጠኞቹ ከድንጋይ ላይ ተቀምጠው በጉልበታቸው እያስደገፉ ዜናና ዝግጅት እያረቀቁ በጋዜጣ ያሳትሙ ነበር፡፡

በ1985 ዓ.ም ቅደመ ውልደቱ ተበሰረ፡፡ በ1987 ዓ.ም ደግሞ ተረግዞ ተወለደ፤ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት፡፡ በእርግጥ በዚህ ስም አልነበረም የተወለደው፡፡ በ1983 ዓ.ም በሀገሪቱ በተደረገው የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ ክልሎች የራሳቸውን መገናኛ ብዙኃን ለማማቋቋም ጥረት አደረጉ፡፡ አማራ ክልልም እንደ ክልል ሲዋቀር የክልሉ ማስታወቂያ ቢሮ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ቢሮው በ1985 ዓ.ም ሲመሠረት በሥሩ የራዲዮና ቴሌቪዥን መማሪያ፣ የፕሬስና የሕዝብ ግንኙነት መመሪያና የዜና አገልግሎት መመሪያዎች ነበሩት፡፡ ቢሮው የራሱ የዜና ማሰራጫ ስላልነበረው ሥራዎቹን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ነበር አሳልፎ የሚሰጠው፡፡ የሽግግር ጊዜው አብቅቶ ክልሎች ሲቋቋሙ የአማራ ክልልም ሰኔ 19 ቀን 1986 ዓ.ም ምሥረታውን አበሰረ፡፡

በዚህ ወቅትም ሐሙስ ሰኔ 19/ 1986 ዓ.ም በኩር ጋዜጣ ስምንት ገጾችን ይዛ በልዩነት ታተመች፡፡ ማስታወቂያ ቢሮው በ1988 ዓ.ም ማስታወቂያ ቢሮ ከባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ተዋሐደ፡፡ በዚህ ውስጥ ሆኖም በቴሌቪዥን ዋና ክፍል፣ በሬዲዮ ዋና ክፍል፣ የፕሬስ ዋና ክፍልና የዜና አገልግሎት ነበር፡፡ እንዲህ ሆኖ ራሱን አልቻለም፡፡ እንደቀደመው ሁሉ ለሌላ ድርጅት እየሰጠ ነበር፡፡ በ1989 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሬዲዮ የአንድ ሰዓት የአየር ሰዓት በመግዛት ‹‹የአማራ ድምጽ›› በሚል መጠሪያ የራዲዮ ስርጭቱን ጀመረ።

ከዓመታት ቆይታ በኋላም በክልሉ ውስጥ የሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ የራዲዮ ስርጭት እንዲኖራቸው አደረገ፡፡ በ1997 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ባደረገው ድጋፍ የራሱን የራዲዮ ጣቢያ ገንብቶ ከጥገኝነት ነጻ በመውጣት የአየር ሰዓቱን ወደ ስድስት ሰዓት ከፍ በማድረግ የራሱን ስርጭት በባሕር ዳር ጀመረ፡፡

ድርጅቱ ማሻሻያዎቹን በማድረግ ሚያዚያ 19/ 1992 ዓ.ም የ30 ደቂቃ የአየር ሰዓት ገዝቶ ከራዲዮ በተጨማሪ የቴሌቪዥን ስርጭት ጀምሮ ነበር፡፡ እርምጃዎቹ ከፍ እያሉ መሄድ ጀመሩ፡፡ ድርጅቱ በ1993 ዓ.ም የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሚል ስያሜ ተቋቋመ፡፡ በ1996 ዓ.ም ደግሞ የቴሌቪዥን ሰዓቱን ወደ አንድ ሰዓት ከፍ በማድረግ ማሰራጨት ጀመረ፡፡ የድርጅቱ መሥራች ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች ያን ዘመን ሲያስታውሱ ‹‹ዜናዎችን ድንጋይ ላይ ተቀምጠን ጽፈን፣ ካሴቶችን በመቀስ አስተካክለን፣ ዜናና ዝግጅቶችን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ የአውቶብስ መናኸሪያ፣ ፖስታ ቤትና ኤርፖርት እንሄድ ነበር፡፡ በዚህ መካከል የሚላከው ካሴት ቢዘገይ ወይም ቢጠፋ የአየር ሰዓቱ ይታጠፋል ወይም ያለፈው ይደገም ነበር›› ነው የሚሉት፡፡ ዓመት ዓመትን እየተካ የኅብረተሰቡም የመረጃ ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ ድርጅቱም የራሱን አቅም እያጎለበተ መጣ፡፡ የኤፍ ኤም ጣቢያዎችን ገነባ፡፡ ስርጭትም ጀመረ፡፡ የቴሌቪዥን የአየር ሰዓቱንም ከፍ እያደረገ መጣ፡፡

ምንም እንኳን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎች ቢኖሩበትም ራሱን ከማሻሻል ግን አልቦዘነም ነበርና የራሱን ስቱዲዮ ገንብቶ የራሱን ስርጭት በራሱ ጀመረ፡፡ የአየር ሰዓታቱንም ከፍ አደረገ፡፡ በደሳሳ ጎጆ በበኩር ጋዜጣ የተጀመረው ጉዞ ራሱን ከዘመኑ ጋር እያዘመነ አሁን በሀገሪቱ ተወዳደሪ ሚዲያ መሆን ችሏል፡፡ ምን ይሄ ብቻ በቅርብ ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች የመረጃ ምንጭ ሆኗል፡፡ በ30 ደቂቃ የተጀመረው ጉዞም 24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ አገልግሎቱም በአማርኛ ቋንቋ ጨምሮ በክልሉ ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች እና ዓለም አቀፉን ቋንቋ እንግሊዘኛን በቴሌቪዥን፣ በራዲዬ፣ በጋዜጣ እና በኦን ላይን ( በአዲሱ ሚዲያ) ለኅበረተሰቡ ተደራሽ ነው፡፡

መናኸሪያ ሄዶ በሰው መረጃ ሲልክ የነበረው ድርጅት ዛሬ ላይ ከዘመኑ ጋር እሽቅድድም በመግጠም በደቂቃዎችና በሴኮንዶች ልዩነት የዓለምን እውነታዎች ለዓለም ሕዝብ በማቅረብ ላይ ነው፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ የነበሩ ሁነቶችንና በተለይም የአርሶ አደሩ ሕይወት እንዲሻሻል በመትጋት በኩል ታላቅ ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ልብ ይበሉ! አሁንም ብዙ ሥራዎች እንዳሉበትም ያምናል፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የራስ ደጀን ተራራ የበለጠ እንዲታወቅና የአውራ አምባ ማኅበረሰብን ዓለም እንዲያውቃቸው በማድረግ በኩል ታሪክ የማይረሳው ሥራም ሠርቷል፡፡ በቅርብ ጊዜ እንኳን ብንመጣ በሀገሪቱ የነበረውን አፋኝና ጨቋኝ ሥርዓት ከሕዝቡ ጎን በመቆም እንዲጋለጥና መልክ እንዲይዝ በማድረግ በኩል የማይደፈረውን ደፍሮ አሳይቷል፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚዲያ መዘመንም ትልቅ ድርሻ ተወጥቷል፡፡

ድርጅቱ በመረጃ እጦት የሚቸገሩ የአማራ ክልል ሕዝቦችና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በተዓማኒነትና በፍጥነት እያደረሰም ይገኛል፡፡ በተለይም ሀሰተኛ መረጃዎች በበዙበት በዚህ ዘመን ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት ብዙዎች አብመድን ይመርጡታል፡፡

ድርጅቱ ብዙ መከራዎችን እየተሻገረ፣ የራሱን መስመር እያሰመረ እነሆ 25ኛ ዓመቱን ሊያበስር ዝግጅት ላይ ነው፡፡ የእናንተ የተደራሲያን አስተያዬት፣ ድጋፍ ለስኬታችን የጀርባ አጥንት ነውና፤ እናመሠግናለን፡፡ አብሮነታችሁም አይለየን፡፡

በታርቆ ክንዴ