ከውጭ ሀገር የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እየሠራ መሆኑን የአዴት የግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡

0
237

ከውጭ ሀገር የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እየሠራ መሆኑን የአዴት የግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአዴት የግብርና ምርምር
ማዕከል ከአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የበጋ መስኖ በኩታገጠም ባለማው የስንዴ ማሣ ላይ የመስክ
ምልከታ ተካሂዷል።
ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ
የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ችባችባሳ ቀበሌ በ27 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እያለማ ነው።
ምርምር ማዕከሉ 65 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል። ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት 40 ነጥብ 5
ኩንታል የቀቀባ ምርጥ ዘር ስንዴ አቅርቧል።
የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ አበዋ በውጭ ምንዛሬ የሚመጣን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ
ምርት ለመተካት የመስኖ ልማት ባለባቸው ሁሉም ወረዳዎች ላይ የስንዴ ቅድመ ማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ስንዴን በመስኖ ለማልማት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በመለየት ለአርሶ አደሮች ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ መገባቱንም
ገልጸዋል።
ምርምር ማዕከሉ ከአፈር ማዳበሪያ ውጭ ሁሉንም ግብዓት በነጻ ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ቁጥር
ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ማዕከሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በባሕር ዳር ዙሪያ እና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች 214 ነጥብ 5 ሄክታር
መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እያለማ ነው ብለዋል። በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ 26 ነጥብ 25 ሄክታር መሬት ላይ የዘር
ብዜት መሆኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጥላዬ ተክለወልድ በክልሉ ከሚገኙ ሰባት የምርምር
ማዕከላት ውስጥ አምስት ማዕከላት በሰብል ላይ ምርምር እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። እ.ኤ.አ በ2023 ከውጭ ሀገር
የሚገባውን የስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የተያዘውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት በአማራ ክልል 13
ሺህ ሄክታር ያህል መሬት በመስኖ ስንዴ ተሸፍኗል ብለዋል።
አርሶ አደር ክንዴ አገኝ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ባመጣው በመስኖ ስንዴ ምርት ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆናቸውን
ነግረውናል። ካሁን በፊት ስንዴ ቢያርቱም ሂደቱን ጠብቀው ባለመዝራታቸውና ተገቢውን ግብዓት ባለመጠቀማቸው ውጤታማ
እንዳልነበሩም ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት ተገቢውን ግብዓት በመጠቀማቸው እና የባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው
የተሻለ ምርት ይጠብቃሉ።
ሌላኛው አርሶ አደር ሀብታሙ ደመም በመስክ ምልከታው ላይ ተሳታፊ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ሀብታሙ የእርሻ ማሳቸው ውኃ ገብ
ባለመሆኑ ስንዴን በመስኖ ማምረት አልቻሉም፡፡ በጉብኝቱ ላይ መሳተፋቸው ግን በቀጣይ የጉድጓድ ውኃ ቆፍረውም ቢሆን ስንዴን
በመስኖ ለማልማት ሀሳብ እንደመጣላቸው ነግረውናል፡፡ የመስክ ምልከታውም ስንዴን ለማልማት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ በ2013 ዓ.ም 1 ሺህ 98 ሄክታር መሬት ስንዴ በመስኖ እየለማ መሆኑን ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት
የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m