ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የተሰጠ መግለጫ

0
1992
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ እድገት፣ ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ አሳታፊ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ክልላችን ቀድሞ ከነበረበት የጦርነት ዳፋ ፈጥኖ ለመውጣት የሚያስችሉ የመልሶ ግንባታ፣ ወትሯዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በአንጻራዊ ውጤታማነት ለማከናወን ተችሏል፡፡
የክልሉን ነዋሪ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት ሁኔታ በማረጋገጥ ረገድ እና በልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች መስክ ከተከናወኑት ውጤታማ ተግባራት ባሻገር ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ በክልላችን ውስጥ በተከታታይነት የተከበሩትና እየተከበሩ ባሉ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን እንደ አብነት መውሰድ ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ከድህረ ጦርነት በኋላ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት በተረጋጋ ሁኔታ ላይ መገኘትን የማይሹ የቀውስ አምባሳደሮች የክልሉን ሕዝብና መንግሥት በግጭት አዙሪት ውስጥ መልሶ ለመዝፈቅ ከመቅበዝበዝ፤ በንጹሃን ዜጎችና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘር አልቦዘኑም፡፡
በፀረ ሰላም ኃይሎች አማካይነት ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 9፡ 00 ሠዓት አካባቢ ጀምሮ በኤፍራታና ግድም ወረዳ ጀውሃ ቀበሌ በሚገኘው የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ እና በፌደራል ፖሊስ አባላቶቻችን ላይ የተፈጸመው ጥቃት የጥፋት ኃይሎች በክልሉ ሕዝብ ላይ የደቀኑት የጥፋት መጠን ለከት አልባነት ያረጋግጣል፡፡
የፀረ ሰላም ኃይሎች በጸጥታ ኃይሎቻችን ላይ የከፈቱትን የአፈሙዝ ላንቃ ወደ ንጹሃን ዜጎች በማዞር በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ እያደረሱም ይገኛል።
በተለይም በኤፍራታ ግድም፣ አጣየ፣ ሰንበቴ፤ ጀውሃ እና በሸዋሮቢት ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ቀበሌዎች የፈጸሟቸውን ጥቃቶች የብሔር መልክ ያለው እንዲመስል በማድረግ በሁለቱ ዞኖች ነዋሪ ሕዝብ መካከል የብሔር ግጭት ለማስነሳት ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራዎችን እየፈጸሙ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ በዚህ የፀረ ሰላም ቡድን እና ተባባሪዎቹ ላይ ሕጋዊ፣ የተጠና፣ በማያዳግም መልኩ የህግ የበላይነትን በማስከበር የክልሉን ሕዝብ ሠላም፣ ደህንነትና አንድነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡
መንግስት ፀረ ሰላም ኃይሎች የከፈቱትን ጥቃት በአጭር ግዜ ውስጥ ለመቆጣጠርና ጥፋተኞችን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌድራል ፖሊስና የአማራ ልዩ ኃይል ፓሊሶችን በስፍራው በማሰማራት መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ያከናውናል፤ እያከናወነም ይገኛል፡፡
ስለሆነም ጥቃቱ በተከፈተባቸው አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝባችን በአካባቢው ከሚገኘው የመንግስት የፀጥታ ኃይሎቻችን የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ አዎንታዊ ሚናውን እንዲወጣ እንጠይቃለን።
በጥፋት ቡድኖች የተከፈተውን ጥቃት የብሔር መልክ በመስጠት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማድረግና መንግሥት ጥቃቱን ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት የማደናቀፍ ተልዕኮ ያነገቡ የአሉባልታ ወሬዎችን የሚያሰራጩ አካላትን በመከላከል ረገድ ሁሉም ነዋሪ ለሰላም ሲባል የድርሻውን አስተዋጽዖ ሊያበረክት ይገባል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ጥቃቱ በተፈጸመባቸው በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ውስጥ በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ የደረሰውን ውድመት እና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ጥቃቱን ለማስቆም፤ አጥፊዎችንም ለህግ ለማቅረብ እና አካባቢውን ቀድሞ ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ የሚደረገውን ጥረትና ዝርዝር ሁነቶች በተመለከተ በተገቢው ወቅት መረጃ የሚሰጥ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።
በመጨረሻም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሕዝብን ሰላም፤ ደህንነትና አንድነት ለማስጠበቅ ቀንና ሌሊት በሚደክሙ የፀጥታ ኃይሎቻችን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሰዉ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎቻችን እና ጥቃጣቸውን በማስፋት በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ በደረሰው ክቡር የሆነ የሰው ህይወት መጥፋትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ምክንያት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለተሰውት የፀጥታ ኃይሎች አባላትና ንጹሃን ዜጎች ቤተሰቦችና ወዳጆች ልባዊ መጽናናትን ይመኛል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ጥር 17ቀን 2015 ዓ.ም
ባሕር ዳር