‹‹ከትናንት ምሽት ጀምሮ የተኩስ ድምፅ አልሰማንም፡፡›› የአጣዬ ከተማ ነዋሪ

0
105

ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2012 ዓ/ም (አብመድ) ከትናንት ምሽት ጀምሮ አንጻራዊ መረጋጋት የተፈጠረ እንደሚመስል አስተያዬታቸውን ለአብመድ የሰጡ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት ከትናንት ምሽት አንስቶ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ የተኩስ ልውውጡ ቆሟል፡፡ ስጋቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቀረፍ ግን መንግሥት ለአካባቢው ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡ “አሁን ተኩስ እየተሰማ አይደለም ማለት ሠላም ሆኗል ማለት አይደለም፤ መንግሥት የችግሩን መሠረት በመለዬት አስቸኳይና ዘላቂ መፍትሔ ይስጠን” ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን የሠላምና ደኅንነት ግንባታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢያለ እንደተናገሩት ደግሞ ማጀቴ፣ ይምሎ እና አላላ በተባሉት አካባቢዎች እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ትንኮሳዎች እንደነበሩ ነው የተናገሩት፡፡ ይህ መረጃ በተጠናቀረበት ጊዜ ግን የልዩ ኃይል፣ የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የጸጥታ ሥጋቱን መቆጣጠራቸውን ነው መምሪያ ኃላፊው ተናገሩት፡፡

ከደብረ ብርሃን ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ሸኖ ከተማ ላይ ትናንት ተዘገቶ በተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ላይ ችግር ተፈጥሮበት የነበረው መንገድም ከሌሊቱ 4፡45 ላይ እንደተከፈተ አቶ እምቢያለ ተናግረዋል፡፡ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ ግለሰቦች ደብረ ብርሃን ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ለኅብረተሰቡ የተሳሳተ መረጃ በመድረሱ መንገዱ ተዘግቶ እንደነበረ የተናገሩት መምሪያ ኃላፊው አሁን ሁኔታዎቹ እየተረጋጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት ሦስት ግለሰቦችም በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን አቶ እምቢያለ ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴው አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግም የልዩ ኃይል፣ የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ኅብረተሰቡን እያረጋጉ እንደሆነ የተናገሩት አቶ እምቢያለ ሁሉም ለሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ ችግሩን በመቅረፍ አካባቢውን ወደ ቀድሞ ሰላሙ ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here