“ከትምህርት ቤቱ ሀገር የሚገነቡ ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ተማሪዎች እንደሚወጡ ሕልሜ ነው” ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው

339

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤታቸው በጎንደር ከተማ ያስገነባውን የሎዛ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ጥቅምት 06/2012 ዓ.ም አስመርቀዋል። በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይም “እኔም እንደናንተው እዚሁ ነው ያደኩት፤ ዛሬ እግዚአብሔር ረድቶን ለዚህ በቅተናል። ደስ ብሏችሁ በማዬቴም በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት እና መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ ለትውልድ የሚተላለፍ ቋሚ ንብረት በመሆኑ ተማሪዎች ንብረቱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መልዕክት ያስተላለፉት ቀዳማዊት እመቤቷ “የትምህርት ቤቱን ንብረት ስታጠፉ ከራሳችሁ ቤት ንብረት እንዳጠፋችሁ ሊሰማችሁ ይገባል፤ ቤታችሁ ላይ ንብረት ላለማጥፋት እንደምትጠነቀቁት ሁሉ ትምህርት ቤቱም ላይ የሚደርስን ጥፋት በመከላከል በተቆርቋሪነት ትምህርት ቤቱን እንድትንከባከቡ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤቷ “ከትምህርት ቤቱ ሀገር የሚገነቡ ትላልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ተማሪዎች እንደሚወጡ ሕልሜ ነው” ሲሉ ተማሪዎች በትምህርታቸው ጠንካራ እንዲሆኑ ምክር ሰጥተዋል። “ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት ነው” ያሉት ቀዳማዊት እመቤቷ የተማረ ዜጋ ሁሌም መልካም ነገሮችን የሚያስብና ሠላምን አጥብቆ የሚፈልግ መሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል። በተለያየ መልኩ የሚፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩም ሠላም ከሌለ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ እንደማይቻልም አስገንዝበዋል።

የሎዛ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በርትተው እንዲማሩ እና የአካባቢያቸውን ሠላም ማስጠበቅ እንዳለባቸው የተናገሩት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ የአካባቢውን ማኅበረሰብም በመተሳሰብና በመረዳዳት ያለውን አስቸጋሪ ጊዜ እንዲያልፉም አሳስበዋል።

የመንገድ መሠረተ ልማት ሳይሟላ የግንባታ ሥራውን በማፋጠንና በተያዘለት የጊዜ ቀጠሮ መሠረት እንዲጠናቀቅ ላደረገው የግንባታ ተቋራጭ አድናቆት እና ምሥጋና አቅርበዋል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ለተማሪዎች ደብተር፣ ‹ዩኒፎርም› እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስም አበርክተዋል። የተገነባውን ትምህርት ቤትም ጎብኝተዋል። ከዚህ በተጓዳኝ የእጅ መታጠብ ቀንም አብሮ ተከብሯል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ