ከባሌና ምዕራብ ወለጋ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው።

0
152

ከባሌና ምዕራብ ወለጋ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሌና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ተውጣጥተው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው።

በባሌ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች ተውጣጥተው ሽኝት የተደረገላቸው ወጣቶች በወቅቱ እንደገለጹት መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ያደረገውን ጥሪ በመቀበል በፍላጎታቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ተዘጋጅተዋል።

ወጣት አቤል ከበደ እንደገለጸው የሀገር ሉዓላዊነት ዓርማ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት አባል ለመሆን በመወሰኑ ደስታ ተሰምቶታል።

“በሀገር ላይ የተቃጣውን የውስጥና የውጭ ትንኮሳ በመመከት ሉዓላዊት ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚጠበቅብኝን የዜግነት ኃላፊነት ለመወጣት በራሴ ተነሳሽነት መከላከያን ለመቀላቀል ወስኛለሁም” ብሏል፡፡

“ጀግኖች አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ለዛሬ የበቃችው ሉዓላዊት ኢትዮጵያ በውስጥና ውጭ ጠላቶች እንዳትደፈር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሴን አሻራ ለማኖር መከላከያን ለመቀላቀል ወስኛለሁ” ያለው ደግሞ ወጣት አህመድ ሙክታር ነው፡፡

“ኢትዮጵያውያን በአራችን ህልውናና ሉአላዊነት ላይ የተቃጣውን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ጥቃት ለመመከት በአንድነት ልንነሳ ይገባል” ብሏል

ወጣቶቹ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ባገኙት ታሪካዊ ዕድል መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የዞኑ የጸጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ገብረዮሃንስ በበኩላቸው “የዞኑ ወጣቶች ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በፍላጎታቸው ለመቀላቀል የወሰኑት ውሳኔ ታሪካዊ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡

የዞኑ ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር እየከፈለ ላለው መስዋእትነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በሽኝት ስነ ስርአቱ ላይ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በተመሳሳይ ከምእራብ ወለጋ ከተለያዩ ወረዳዎች ተውጣጥተው የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

ወጣቶቹ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት “መከላከያ የሀገሪቱ መከታና ሉዓለዊነት ምልክት ነው፤ እኛ ደግሞ የሀገሪቷ መከታ ለሆነው መከላከያ ሠራዊት አባል ለመሆን ስንወስን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል” ብለዋል፡፡

“ባለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን የራሱ ብቻ አድርጎ ሲገዛ የቆየው ጁንታ አሁንም እኔ ካልገዛሁ እያለ እየተፍጨረጨረ ይገኛል፤ ይህ ደግሞ መቼም አይቻልም” ያሉት ወጣቶቹ “የጁንታውን ጥቃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቀልበስ ተዘጋጅተናል፤ በተግባርም እናሳያለን” ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍ ለነጋችን ስንቅ እየሆነልን ነው፤ እኛም እንደ ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ለሀገራችን ሉዓለዊነትና አንድነት ለመቆም ዝግጁ ነን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ኡማታ “ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ውስጣዊና ውጫዊ ጫና ለመከላከል እንደ ሌሎች ሀገር ወዳድ መከላከያ ሰራዊት በወኔ እንደምትሰሩ አልጠራጠርም፤ ድል ከናንተ ጋር ይሁን” ብለዋል፡፡

በሽኝት ስነ ስርአቱ ላይ በየደረጃው የሚገኙ የዞኑ አመራሮችና አባ ገዳዎች ተገኝተው ወጣቶቹን በምርቃት መሰናበታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here