ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ ለሰፈሩ ዜጎች የበጎ አድራጊ የህክምና ባለሙያዎች የሕክምና አገልግሎት እየሠጡ ነው፡፡

0
31

ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ ለሰፈሩ ዜጎች የበጎ አድራጊ የህክምና ባለሙያዎች የሕክምና
አገልግሎት እየሠጡ ነው፡፡
ህክምናውን ‘ፈውስ’ የተባለ የሕክምና በጎ አድራጎት ማኅበር ነው እየሰጠ የሚገኘው፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወይዘሮ እናት ይመር ከመተከል ዞን ከተፈናቀሉት ዜጎች ውስጥ አንዷ ናቸው።
ባጋጠማቸው የጤና እክል ምከንያት ነጻ የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ሕክምናው ባይኖር ኖሮ አይኔን
እስከወዲያኛው ላጣ እችል ነበር” ያሉት ወይዘሮዋ የህክምና አገልግሎቱን በማግኘታቸውም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሌላው ተፈናቃይ ዓባይነህ አበበ ይባላሉ፣ የጤና ቡድኑ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የተፈናቀሉበት ጣቢያ ድረስ
በመገኘታቸው ምስጋና አቅርበዋል። በነፃ የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።
በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ የሕክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ባለሙያዎች ውስጥ በክሊኒካል ነርሲንግ የተሰማራችው ሞሚና
አበበ አንዷ ነች። በሙያዋ አገልግሎት በመስጠት የተፈናቀሉ ወገኖቿን እያገለገለች እንደሆነ ተናግራለች።
በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሠራተኞች የተቋቋመው ‘ፈውስ’ የሠራተኞች በጎ አድራጎት ማኅበር፣ በክልሉ
ጤና ቢሮ አጋዥነት ፤አጋር ተቋማትና ግለሰቦችን በማስተባበር ተፈናቃዮቹን በሕክምናው ዘርፍ እየደገፉ ነው።
በማኅበሩ ውስጥ የታቀፉ 24 የሕክምና ባለሙያዎች መጋቢት 06/2013 ዓ.ም ወደ ቻግኒ በማቅናት ለተፈናቃዮቹ የሕክምናና
የምክር አገልግሎት እየሠጡ እንደሚገኙ የሕክምና ቡድኑ አስተባባሪ መልካሙ ባዬ (ዶክተር) ተናግረዋል። የቡድኑ አባላት የቀዶ
ጥገናን ጨምሮ የውስጥ ደዌ እና የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎችን ያቀፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ 52 ሺህ ብር የሚገመት የመድኃኒት አይነቶችንና የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሣቁስ በመያዝ ወደ ጣቢያው የተንቀሣቀሰ
መሆኑን የተናገሩት ዶክተር መልካሙ ለአምስት ቀናት የሚቆይ አገልግሎት እንደሚሠጡም አስረድተዋል። በቆይታቸው የሕክምና
አገልግሎት ፍላጎትን በመለየት በቀጣይ ለሚተካቸው የጤና ቡድን በጥናት ላይ የተደገፈ የመረጃ ግብዓትን በመስጠት
ሕክምናው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ተፈናቃዮቹ የግል ንጽህናን ለመጠበቅ አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩ ህፃናትና አዛውንቶችን ጨምሮ አብዛኞቹ ታካሚዎች የዓይንና የቆዳ
በሽታ ተጠቂዎች ሆነዋል” ያሉት የሕክምና ቡድኑ አስተባባሪ የበሽታው ሁኔታ ከጠበቁት በላይ እንደሆነ ነግረውናል።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ – ከቻግኒ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here