“ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም እያሉ ለሚያወዛግቡ ኃይሎች የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ቦታ እንደማይሰጡ ርእሰ መሥተዳድሩ አስታወቁ።

312

ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2013ዓ.ም (አብመድ) “የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ስጋት የሆኑ አካላትን ቀድሞ በመከላከል ሕዝባዊ አደራቸውን ይበልጥ መወጣት አለባቸው” ሲሉ ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ አስታወቁ።

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ለከፍተኛ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች እጀባና ጥበቃ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል።

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አንማው ዓለሜ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ብቃት ያለው ፖሊስ መገንባት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ በተለያዩ ዙሮች በአካል ብቃት የዳበረና ተልእኮን በቁርጠኝነት የሚተገብር ኃይል እያሰለጠነ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ “የአማራ ሕዝብ ከድህነት ወጥቶ ሰላሙ እንዲረጋገጥና የሀገር አለኝታነቱ እንዲቀጥል ጠንካራ መንግሥት ያስፈልገዋል” ነው ያሉት።

የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ “የአማራ ፖሊስ ሪፎርም እንዲያደርግና ሕዝባዊ አደራውን እንዲወጣ ያደረጉት ድጋፍ ጉልህ ለውጥ አስመዝግቧል” ያሉት ኮሚሽነሩ የአማራ ፖሊስ ለሀገር አርአያ ሆኖ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ደግሞ ክልሉን ሰላም የተረጋገጠበት እንዲሆን በተደረገው ጥረት የአማራ ፖሊስ ጉልህ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

የአማራ ፖሊስ በየጊዜው አቅሙን እያሳደገ ሕዝባዊ ታማኝነቱን ይበልጥ እንደሚያረጋግጥም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

“ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም እያሉ ለሚያወዛግቡ ኃይሎች የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ቦታ የለንም፤ ዛቻና ማስፈራሪያቸውም አያሰጋንም” ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ። “ሰላማዊ የሆነውን የአማራ ክልል ‘ባለአደራ መንግሥት ሊቋቋምለት ይገባል’ እያሉ በሕዝብ ዘንድ መደናገር ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎችንም ፍላጎታቸውን ስለምናውቅ ከሕግ ውጭ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም አካል ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

ይልቁንም “ከመስከረም 30 ጀምሮ የዘራነውን እሸት የምንበላበት፤ እንጅ የምንታመስበት አይሆንም። ምክንያቱም ጠንካራ መንግሥትና ሕዝብ ስላለን” ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። የፖሊስ ኃይሉም በማሰልጠኛ ተቋማት በሚተገበሩ ስልጠናዎች በመታገዝ ተልእኮውን በብቃት እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው እሸቴ -ከደብረ ማርቆስ