“እውነትን የመካድ ዘመቻ”

0
199

“እውነትን የመካድ ዘመቻ”
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከዓባይ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ግብፅ እና
ሱዳን ከወትሮው በተለየ ጫና ለመፍጠር በአንድ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ በቀጣዩ የክረምት ወቅት ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር
የውኃ ሙሌት ስትጀምር ሁለቱ ሀገራት ሙሌቱን ለማስተጓጎል አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ የማይፈነቅሉት ቋጥኝ ይኖራል ተብሎ
አይገመትም፡፡
ከምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት መካከል እንደነገሩ የቆመ የሽግግር ሀገረ መንግሥት ያላት እና በውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻ
የምትናጠው ካርቱም ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዑመር አልበሽር በኃይል መወገድ በኋላ ውስጣዊ ችግሮቿን ለማከም በጎረቤቶቿ
ድንበር አካባቢ ማንዣበብን አማራጭ አድርጋ ይዛዋለች፡፡ ሱዳን ምንም እንኳን የዓባይ ጉዳይ በኃይል ሊፈታ እንደማይችል
ብታውቅም የሱዳናውያንን ቀልብ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ለማውጣት የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ እፎይታ የሚሰጥ አማራጭ
አድርጋ ያየችው ትመስላለች፡፡ ለዚህ ማሳያው ከወራት በፊት ለዘመናት የቆየ ድንበር ጥሳ የመሬት ወረራ በኢትዮጵያ ላይ መፈጸሟ
ነው፡፡
ኢትዮጵያውንን እና ኢትዮጵያን በውል የማይረዱ ጎረቤቶቿ ሁልጊዜም የሚስቱት አንድ ነገር አለ፡፡ የቱንም ያክል ውስጣዊ ልዩነት
እና ድክመት ቢኖርባቸውም በብሔራዊ የሀገር ክብር እና ጥቅም ጉዳይ ግን በጋራ ያልቆሙበት ጊዜ አለመኖሩ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በደማቁ የተጻፉ በርካታ አኩሪ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ቢሆኑም በጥቁር ነጥብ የተመዘገቡ የታሪክ ክስተቶችንም
አሳልፈዋል፡፡ ታዲያ በእነዚህ የጨለማ ዘመናት ውስጥ እንኳን በጋራ መቆም እና በጎ ነገሮችን የሚያጎሉ ተግባራትን በኅብረት
መፈፀም በትምሕርት ሳይሆን በተፈጥሮ የተቸሩት ፀጋ ነው፡፡
አፍሪካ ውስጥ በቂ የውኃ ክምችት አላቸው ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር
በ2013 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት ከ80 አስከ 90 በመቶ ገደማ የሚሆነው የሀገሪቱ የውኃ ፀጋ በአራት ታላላቅ ወንዞች
ማለትም ዓባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ አኮቦ እና ኦሞ ጊቤ ወንዞች ተከማችቶ የሚገኝ ነው። አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል 70 በመቶ
የሚሆነውን ውኃ የሚያገኘው በክረምት ሦስት ወራት ከሚዘንበው ዝናብ ነው፡፡ ይህ ሃብት ሀገሪቱ ልታመነጨው ከምትችለው 45
ሺህ ሜጋ ዋት ገደማ ጠቅላላ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 67 በመቶ ወይንም 30 ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት
የሚያስችል ነው፡፡
ኢትዮጵያ 45 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በተፋሰሱ ውስጥ የሚኖር ሲሆን በአጠቃላይ 90 በመቶ የተፋሰሱ ነዋሪ ቀጥታ ተጠቃሚ
መሆን የሚችልበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ላይ ይገኛል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግዙፍ የኃይል አቅርቦት
አማራጭና የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በቀጥታ የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ በተዘዋዋሪ ደግሞ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር
በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብና ሥራ እንዲፈጠርለት የሚማፀን ወጣት እንዲሁም በኃይል እጥረት ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቷን
የምትነጠቅ እናት የሚሹት ነገር ነው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የዓባይ ወንዝ ለዚህ ዘመን ትውልድ የሀገር ክብርን እና ሉዓላዊነትን ታሳቢ ያደረገ ዓርማ ሆኗል፡፡ የግብፅ
በኢትዮጵያ ላይ መነሳት አዲስ ነገር ሳይሆን የቆየ እና ዘመናትን የተሻሻገረ ነው፡፡ የሁለቱ ሀገራት መልካም እና ታሪካዊ የሆኑ
ግንኙነቶቻቸው እንዳሉ ሆነው የጉንደት እና ጉራዕን ጨምሮ አሥራ አንድ ጊዜ ጦርነት ተደርጎ ግብፅ በኢትዮጵያ አይቀጡ ቅጣት
ተቀጥታ ተመልሳለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በግብፅ ጳጳሳት መተዳደር ምክንያት ግብፅ ታደርሰው የነበረው ሃይማኖትን የታከከ
ተፅዕኖ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፍፃሜ አግኝቷል። የዓባይ ወንዝ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት እንዲሻክር ካደረጉት
መልክዓ ምድራዊ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ነው። የጥንት ኢትዮጵያ ነገሥታት በተለያዩ ጊዜያቶች የዓባይን ወንዝ ለመገደብ
ሙከራ ያደርጉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ትከተለው የነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት እየተዳከመ ሲመጣ የግብፅ መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ
ያለኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ግድብ በመገንባቱ ትልቅ ቅሬታን የፈጠረ ክስተት ሆኖ አለፈ። ነገሮች ሳይሞቁ እና ሳይቀዘቅዙ
ኢትዮጵያውያን የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ረጅም ዘመናትን በዝምታ ማሳለፋቸውም የዓባይ ጉዳይ “የተበላ እቁብ”
የመሰላቸው ፈርኦናውያን መሪዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ 6 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል ግድብ ለመሥራት መፈለጓን እውን
ካደረገች ከ2003 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት እንደገና እየሻከረ መጣ። በተለይም የአረቦች ፀደይ የማኅበራዊ
ሚዲያ አብዮትን ተከትሎ ግብፅን ማስተዳደር የጀመረው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ መሪ ሙሃመድ ሙርሲ የተለመደው
የግብፃውያን የተፈጥሮ የዓባይ ውኃ ባለቤትነት ልብወለድ ታሪክን ካቆመበት አስቀጠሉ፡፡ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሳይቀር
ሙሃመድ ሙርሲ “ከዓባይ ወንዝ አንዲት ጠብታ ብትጎድል ግብፃውያን ደማቸውን ለማፍሰስ ዝግጁ ናቸው” ማለታቸው ደግሞ
የሁለቱ ሀገሮች የዲፕሎማሲ ውጥረት ዳግም እንዲያገረሽ አደረገ።
የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በሦስቱ ሀገሮች መካከል በተለያየ ጊዜ በተለያየ አኳኋን
ውይይቶች ቢካሄዱም ስምምነት ላይ መድረስ ግን አልተቻለም። ግብፅ ግብፃውያንን ብቻ ሳይሆን ሱዳናውያንን እና ቀሪው
የዓለም ክፍልን በኢትዮጵያ ላይ መነሳት እንዲችል የማታሰራጨው ሃሰት፣ የማትዘራው ውሸት እና የማታምታታው እውነት የለም፡፡
በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከተራራ የገዘፈ ሀቅ እና እውነታ ቢኖራትም በተሳሳተ መረጃ የተበረዘውን ቀሪ የዓለም ክፍል ለማስረዳት የጋት
ያክል እንኳን የተራመደች አትመስልም፡፡ እንደ ሲሳይ ዓለማየሁ እና ሙሃመድ አል አሩሲ የመሰሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን
የሚያደርጉትን የዓባይ ውኃ የአርበኝነት ዘመን ተጋድሎ በተቋማት እና በመንግሥት ድጋፍ ካልተረዳ በስተቀር ሩቅ የሚያስጉዝ
ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለም፡፡ 150 ሚሊዮን ግብፃውያንን ኢትዮጵያ በጉሮሯቸው ላይ ቆመች በሚል ዓለምን የምታሳስተውን
ግብፅ ያክል 60 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በጭስ እንደሚሰቃዩ እና በዚህ ዘመን በጨለማ ውስጥ እንደሚኖሩ የሚያስረዳላቸው
እና የሚጮህላቸው እንኳን የለም፡፡
ኢትዮጵያን ለምትከሰው ግብፅ በዓባይ ለመጠቀም ዓባይን በጋራ ማልማት እንደሚያስፈልግ የሚጮህ እና ዓለምን የሚያስረዳ
አርበኛ ያስፈልጋል፡፡ አሁናዊዋ ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም ፈተናዎች በዝተውባታል፡፡ ያለፉትን የሚመስሉ ጥቁር የታሪክ
አጋጣሚዎች ከዚህም ከዚያም ተዘርተው እና በቅለው እየታጨዱ ተስተውለዋል፡፡ ነገር ግን በጥቁር ታሪክ ወቅት የሚደምቅ በጎ
ኅብረት የኢትዮጵያውያን መለያ ነውና በጋራ ለመቆም እና ነገን ለማማተር ጉልበት ይሆናል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here