“እኛ ዛሬ የምናስቀምጠው ጡብ የነሱን የነገ ቤት ይገነባል” እሸቱ በቀለ (ዶክተር)

0
68

ኢትዮጵያውያኑ ከአጣዬ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ለገቡ 12 ተማሪዎች ሙሉ ዓመታዊ ወጪን ለመሸፈን ቃል ገቡ፡፡

ሌሎች 85 ተማሪዎች ግን አሁንም ድጋፍ ይሻሉ ተብሏል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሕሊናቸውን በፍቅረ ነዋይ የለወጡ የሕዝብን ሰላም ለመንሳት ሌት ከቀን ያቅዳሉ፣ ስምሪት ያደርጋሉ፣ እኩይ ዓላማቸውን ለመተግበር የሚያስችላቸውን ስልት ሁሉ ተጠቅመው ተማሪዎች እቅዳቸውን እንዳያሳኩ አዕምሯቸውን በጥላቻ ይመርዛሉ፣ ነጋዴዎች እንዳያተርፉ፣ አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ተረጋግተው ሕይወታቸውን እንዳይመሩ፣ ሰዎች በየአካባቢያቸው በሰላም እንዳይንቀሳቀሱ፣ መንግሥትም ትኩረቱን ወደ ልማት እንዳያዞር ሴራ ይጠነስሳሉ፡፡

ለጥቅም የተገዙ የክፋትን ነዋይ የሚሹ፣ ሕሊናቸውን ሸጠው በፍቅረ ነዋይ የሰከሩ፣ የሰው ደስታን በመንጠቅ የሚረኩ ፍጡራን ቢኖሩም ነገን የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚሹ ደግሞ ችግርን ተጋፍጠው የተስፋ ጭላንጭልን አሻግረው ይመለከታሉ፤ እኩይ ሴራዎችን በብልሃት አልፈው ስኬትን ያልማሉ፤ ራዕያቸውን እውን ለማድረግም ይተጋሉ፡፡

 

ተማሪ አዲሱ አብተው የሕዝብን ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች የፈጠሩት የሰላም መደፍረስ ዓይኑን ከትምሕርቱ እዲነቅል አላደረገውም፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ያጠናቀቀው ተወልዶ ባደገባት አጣዬ ከተማ ነው፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ከፍተኛ ትምሕርት ተቋም በከፍተኛ ውጤት ገብቷል፡፡ የራሱ ብርቱ ጥረት እንዲሁም የቤተሰቡና የመምህራን ከፍተኛ ድጋፍ የውጤታማነቱ ምስጢር ናቸው፡፡

ተማሪ አዲሱ አጣዬና አካባቢዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርቱን በአግባቡ እንዳይከታተል አድርጎት ቆይቷል፡፡ የትምህርቱ መስተጓጎልም ከፍተኛ የሥነልቦና ጫና እንደፈጠረበት ነው የተናገረው፡፡

ይሁን እንጂ ችግሩ ፈጽሞ ከዓላማው አላደናቀፈውም፤ ችግሮችን እንደ አንድ የሕይወት አጋጣሚ ቆጥሮ ጫናውን ለመቋቋም ጥረት አድርጓል፤ የጥናት መርኀግብር አውጥቶም በርትቶ አንብቧል፤ ውጤታማነቱንም አስጠብቋል፡፡ ተማሪ አዲሱ ጥቅመኞች በፈጠሩት ጊዜያዊ ችግር ውስጥ ነገውን የተሻለ ለማድረግ ትኩረቱን ወደ ጥናት በማድረግ በ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተናው 651 ነጥብ አምጥቷል፤ ፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ እንቁ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ተርታ ለመሰለፍም በቅቷል፡፡

አሁን ተማሪው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ትምህርቱን እየተከታተለ ነው የሚገኘው፡፡ የሕክምና ዶክተር ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ፍላጎት እዳለው ተናግሯል፡፡ በሚሠማራበት የሙያ ዘርፍ ጠንክሮ በመሥራት ለሀገሩ የድርሻውን ለማበርከትም በዩኒቨርሲቲው ጠንክሮ እደሚማር ነው የነገረን፡፡

በሀርቫርድ ዩንቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ዕውቅና እንዳተረፉ የሚነገርላቸው አንድ ኢትዮጵያዊ የተማሪውን ወጪ ለመሸፈን ቃል መግባታቸው ተሰምቷል፡፡ እኒህ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር መኮንን ያሬድ ይባላሉ፤ የቀድሞ የደብረብርሃን ተማሪዎች ሕብረት አባል ሲሆኑ የተማሪውን የአንድ ዓመት የትምህር ወጪ ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን ቃል መግባታቸው ነው የታወቀው፡፡

አጣዬና አካባቢዋ በተፈጠረው ግጭት የተማሪ አዲሱና የጓደኞቹ ወላጆች ቤትና ንብረት ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በአስቸጋሪው ጊዜ ድጋፍ ማግኘቱ ትኩረቱን በትምህርቱ ላይ እንዲያደርግና ካሰበበት ለመድረስ እደሚያስችለው ተናግሯል፡፡

በወላጆቹ ዘንድ ሊያጋጥም የሚችል ምጣኔ ሀብታዊ ችግርን ስለሚያቃልል ድጋፉ በጣም አስፈላጊ ነው ብሏል ተማሪ አዲሱ፡፡

የቀድሞ ደብረብርሃን ተማሪዎች ሕብረት ገዘፍ ያለ ሀገራዊ መዳረሻ ይዞ በመመስረት ላይ ያለ ማኅበር ሲኾን የአንድ ዓመት እድሜ እንኳን አላስቆጠርም፡፡ በውጪ ሀገራትና በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሕብረቱ አባላት ከአጣዬ አካባቢ ወደ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉ 12 ተማሪዎችን ሙሉ ወጪ ለመሸፈን ወስነዋል፡፡ የትራንስፖርትን ወጭ ጨምሮ ሙሉ የዓመት ወጪያቸውን ለመሸፈን ነው ቃል የገቡት፡፡

የማኅበሩ ጊዜያዊ ሰብሳቢ እሸቱ በቀለ (ዶክተር) እንዳሉት ከዚያ አካባቢ ወደ የኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች የቤተሰቦቻቸው ሀብትና ንብረት የወደመባቸው ናቸው፡፡ በአጣዬ ከ85 በላይ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡ ሲኾን ሁሉም ድጋፍ እንደሚሹ ዶክተር እሸቱ ተናግረዋል፡፡

የሕብረቱ ስብስብ ለመጓጓዣና ለአንዳንድ ወጪዎች ገንዘብ ከመደገፍ ውጪ የ12 ተማሪዎችን ዓመታዊ ወጪ ብቻ የመሸፈን አቅም ነው ያለው፡፡

“እኛ ዛሬ የምናስቀምጠው ጡብ የነሱን የነገ ቤት ይገነባል” ያሉት ጊዜያዊ ሰብሳቢው የ12 ተመናሪዎች የአንድ ዓመት እንቅስቃሴ እየታየ ድጋፉ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው መርዳት በሚችሉበት ደረጃ እስኪቋቋሙ ድረስ ግን ለሌሎቹ ተማሪዎችም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አብራርተዋል፡፡ አሁን በግለሰብ ደረጃ ድጋፍ ለማድረግ ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ ስለመኖራቸው በማንሳትም ባለሀብቶች፣ ረጂ ድርጅቶችና ልዩልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here