“እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነን፤ ታሪክ እንሠራለን እንጅ ታሪካዊ ስህተት አንፈጽምም” የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሣኅሉ (ዶ.ር)

0
71
“እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነን፤ ታሪክ እንሠራለን እንጅ ታሪካዊ ስህተት አንፈጽምም” የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሣኅሉ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
በሰልፉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሣኅሉ (ዶ.ር) ሽብርተኛው ትህነግ የመላው ኢትዮጵያ የጋራ ጠላት ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ በመድረስ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ ዳግም ጦርነት ማወጁን አንስተዋል፡፡ በዚህም በአማራ እና በአፋር ክልል ያደረሠው ጥቃት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የትህነግ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያ ጠላት በመሆኑ ዛሬም ሕጻናትን እና አረጋውያንን ለጦርነት አሠልፎ እያወጋ እንደሚገኝ ዶክተር ድረስ ገልጸዋል፡፡
በሴራ ተወልዶ በሴራ ያደገው ሽብርተኛው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ከቀን ከሚታትሩ የውጭ ኀይሎች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡
ሁሌም በእኛ ሳንባ ተንፍሱ የሚሉት የውጭ ኃይሎች የተጽዕኖ በትራቸውን በእኛ ላይ ለማሳረፍ ሽብርተኛው ትህነግን በፈረስነት ተጠቅመውበታል ነው ያሉት፡፡
ምዕራባውያን ሽብርተኛው ትህነግ ሕጻናትን እና አረጋውያንን ለጦርነት ሲያሰልፍ ፣ ማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ ሲፈጽም ዝምታን የመረጡት መልሶ እንዲያንሰራራ ካላቸው ፍላጎት አንጻር ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ድረስ የውጭ መንግሥታት በሽብርተኛው ትህነግ የሥልጣን ዘመን የኢትዮጵያን መንግሥት በሰብዓዊ መብት እና በዲሞክራሲ ጥሰት ሲከሱ እንዳልነበር ሁሉ ዛሬ ለሽብርተኛው ቡድን ዋስ ጠበቃ መሆናቸው ተስተውሏል ነው ያሉት፡፡
ዶክተር ድረስ የውጭ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር የከፈቱብንን ሁሉን አቀፍ ጦርነት አንድነታችንን ከምንጊዜውም በላይ በማጠንከር ልንፋለም ይገባል ብለዋል፡፡ በአንድነት አሸባሪ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ የሴራ ፖለቲካውን ሲዘራ ቢቆይም “እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል” እንዲሉ ተንኮሉን ተረድተናል ብለዋል፡፡ ለዚህ ተንኮል እና ሴራ ፍጹሞ እጅ አንሠጥም፡፡ የዛሬው የድጋፍ ሠልፍ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ይዟል፤ አንድም አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን አቋማችንን ማሳያ ሲሆን ሁለተኛው ለዚህ አፍራሽ ቡድን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድጋፍ ለሚያደርጉ ሀገሮች ለአሸባሪው ድጋፍ መስጠት ነውርም አሳፋሪም መሆኑን ተገንዝበው እጃቸውን እንዲያነሱ ለማሳሰብ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ የሚደረገው ዘመቻ የህልውና ዘመቻ ነው፤ ማንኛውም ነዋሪ ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች በማበር የአማራን ብሎም ኢትዮጵያን ጠላት መፋለም ይገባል ነው ያሉት፡፡
ልዩነት ለማንጸባረቅ፣ ፖለቲካ ለማራመድ፣ ሃይማኖትን ለመስበክ፣ ነግዶ ለማትረፍ ሀገር ያስፈልጋል፤ ስለዚህ ለሀገራችን ዘብ ልንቆም ይገባል ብለዋል ዶክተር ድረስ፡፡
”እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነን፤ ታሪክ እንሠራለን እንጅ ታሪካዊ ስህተት አንፈጽምም፤ ስለሆነም የክልላችን ነዋሪዎች የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል የአርበኝነት ገድል ለመፈጸም ወደ ግንባር እንድተም ጥሪየን አቀርባለሁ“ ብለዋል፡፡
በትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here