እንፍራንዝ ሰላሟን ታስጠብቃለች፡፡

0
47

እንፍራንዝ ሰላሟን ታስጠብቃለች፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ የተጻፈባት፤ ቤተመንግሥት የታነጸባት፤ የሊቃውንት መሰብሰቢያ ጉባኤ መገኛ፣ የደረሰ ሁሉ በፍቅር የሚስተናገድባት፣
የሃይማኖቶች ብዝኀነትን በፍቅር አስተሳስራ የዘለቀች የአብሮነትና የፍቅር፣ የወንድማማችነትና የመተሳሰብ ከተማ፣ የአፄ ሰርጸ ድንግልን ቀልብ የማረከች፣ በደርግ ዘመነ
መንግሥት ወታደራዊ ስትራቴጂክ ቦታ የነበረች፣ ጉዛራ ቤተ መንግሥትን እንደ ዘውድ የተከናነበች ባለታሪክ ከተማ ናት። ቅንጡ ህንጻዎችና ግንባታዎች ባይታዩባትም ሁል
ጊዜ ደምቃ ትታያለች– እንፍራንዝ።
የጥንት ገናና ታሪክ ባለቤቷ እንፍራንዝ የማይነጥፍ ባሕል ባለቤት ናት።
ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት ነውና ነዋሪዎቿ አሁንም ስለ ሰላም አይቦዝኑም።
እንፍራንዝ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም ችግር አስተናግዳለች። በከተማዋ ተገኝቶ ሂደቱን እየተከታተለ የሚገኘው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ስለምርጫው ሂደት፣
ስለ ፍትሐዊነቱ፣ በነጻነት ስለመካሄዱና ከምርጫ በመለስ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት ጠይቋል።
ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፣ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የተካሄደ፣ መራጮች ይወክለኛል ላሉት አካል ያለጣልቃ ገብነት ድምጽ የሰጡበት፣ ዴሞክራሲያዊና በብዙ መመዘኛ
ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ምርጫዎች የተሻለ መኾኑን መምህር አምባዬ ሙጬ ነግረውናል።
ምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የምርጫ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና የጸጥታ አካላትም ሂደቱ ተዓማኒ እንዲኾን የሚጠበቅባቸውን ተወጥተዋል ነው ያሉት መምህሩ።
ከምንም በላይ ሕዝቡ ሰላም ወዳድ በመኾኑ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን ነው ያነሱት። በምርጫ ጣቢያ ደረጃ የመራጮች ጊዜያዊ ድምጽም ዛሬ ይፋ ተድጓል።
ከምርጫ በኋላ የከተማዋ አስተማማኝ ሰላም እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል ያለው ደግሞ ወጣት አሰፋ ብርሃን ነው። “ሰላም ከሌለ መጀመሪያ የምንጎዳው እኛ ወጣቶች ነን።
ስለዚህ ሀገር ሰላም እንድትኾን ከፍተኛውን ድርሻ መወጣት ያለብን ወጣቶች ነን” ብሏል።
በተለይ ምርጫውን ተከትሎ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠርና የሀገር ሰላም እንዳይናጋ ከጸጥታ አካላት ጋር በመኾን የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መኾኑን
ተናግሯል።
በምርጫ ሂደት አብላጫ ድምጽ ማግኘት ወይንም አለማግኘት የሚጠበቅ ነው። የምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን አብላጫ ድምጽ ያገኘውን አካል በጸጋ መቀበል
እንደሆነም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግፈዋል።
ለዚህም የሕዝቡን ሰላም ወዳድነትና በተለይ ወጣቱ በተደራጀ አግባብ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
የሀገር ቀጣይነት፣ ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ ማግኘት፣ ነግዶ ማትረፍ እና ወልዶ መሳም የሚረጋገጠው ሀገር ሲኖር ነው። በመኾኑም የሕዝብን ሕልውና የሚፈታተን አንዳች
ነገር እንዲኖር አንፈቅድም ብለዋል የእንፍራንዝ ከተማ ነዋሪዎች።
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ-ከእንፍራንዝ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here