እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአዊ ቋንቋ ባሕልና ታሪክን ለማሳደግ የሚያስችል ማዕከል ለመክፈት እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።

0
126

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአዊ ቋንቋ ባሕልና ታሪክን ለማሳደግ የሚያስችል ማዕከል ለመክፈት እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የቋንቋ፣ ባሕልና ታሪክ ማበልጸጊያ ማዕከል ለመክፈት የሚያስችል ሲፖዝየም ዛሬ
በእንጅባራ ከተማ እየተካሄደ ነው። በሲምፖዚየሙ የመክፈቻ ንግር ያደረጉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ባይነሳኝ
ዘሪሁን የአዊ ሕዝብ ከክልሉ ሕዝብ ጋር የሚጋራቸው በርካታ ልምዶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
ለዘመናት ጠብቆ የቆየው የራሱ የኾነ ባሕላዊ ትውፊት፣ አለባበስ፣ ዕውቀት፣ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት፣ የዕደ ጥበብ
ውጤቶች፣ ባሕላዊ ሙዚቃ፣ ስልተ ምርት እና ቋንቋ ያለው ሕዝብ ነው ብለዋል። ሕዝቡም ሕግ አዋቂ ብቻ ሳይሆን በሕግ
አክባሪነትም የሚታወቅ እንደሆነ ነው ዋና አሥተዳዳሪው የገለጹት፡፡
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጋር በመኾን የአዊ ቋንቋን፣ ባሕልና ታሪክ ለማሳደግ የባሕል ማዕከል ከፍቶ
ለመሥራት ዝግጅት ማድርጉ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል። ብሔረሰብ አሥተዳደሩም በቅንጅት እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ።
የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት አዕምሮ ታደሰ (ዶክተር) የአዊ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ሳይበረዝ ትክክለኛ
ይዘቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ማዕክሉን ለመክፈት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ማዕከሉ በአዊ ባሕል፣
ቋንቋ እና ታሪክ ላይ ምርምሮች የሚሰሩበትና ጥቅም ላይ የሚውሉበት ነው ተብሏል፡፡
የአዊ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሀብቶች የሚሰባሰቡበት፣ የሚደራጁበት እና የሚጠበቁበት እንዲሁም መረጃዎች በአግባቡ
የሚሰነዱበትና ጥቅም ላይ የሚዉሉበት ይሆናል፡፡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚፈልቁበት እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡
በውይይቱ የተገኙት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አሥተዳደር ተመራማሪና መምሕር አለማየሁ እርቂሁን (ዶክተር)
ዩኒቨርስቲው እንዲህ ዓይነት ሥራ መጀመሩን አድንቀው የቀረቡ ሰነዶች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ስያሜውም ታሪካዊ
እንዲሆን አስተያየት ሠጥተዋል፡፡
ሌላዋ አርቲስት እና የሙዚቃ መምሕርት ካሰች አማረ በዩኒቨርስቲው የሚከፈተው የባሕል ማዕከል ሙያቸውን ለማሳደግና
የአካባቢውን ባሕል፣ ቋንቋና ታሪክ ለማጎልበት ከፍ ያለ ድርሻ ይኖረዋል ብላለች።
በሲምፖዚየሙ የሰላምና ደኅንነትን ሚኒስቴር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶክተር)፣ የኢፌዴሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥበቃ
ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበበ አያሌው፣ የቀድሞ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይ፣
አርቲስት አያልነህ ሙላቱና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ምትኩ (ዶክተር)፣ ጥሪ የተደረገላቸው
እንግዶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው – ከእንጅባራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m