“እነኾ የማይጠፋው ብርሃን ወጥቷል”

35
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ወልድያ: ታኅሣሥ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም በድቅድቅ ጨለማ ተከባለች፣ ሲኦል በሯን ከፍታ ነብሳትን ትውጣለች፣ በእሳቷ ትገርፋለች፣ በንፍር ውኃዋ ትጠብሳለች፣ ምድር በትዕቢተኞች እና በአመጸኞች ተመልታለች፡፡ ያልተገባን መሻት ቁጣን አምጥታለች፣ ከገነት አስባርራለች እና መከራው ጸንቷል፡፡ ብርሃን የለበሱት ጨለማ ለብሰዋል፣ በጨለማ ካባ ተጠቅልለዋል፣ የተከበሩት ተዋርደዋል፣ ከፍ ከፍ ያሉት ዝቅ ብለዋል፣ ዝምታ ባለበት፣ መንፈስ ቅዱስ በመላበት ሥፍራ ይኖሩ የነበሩት ዋይታና ለቅሶ በበዛበት ሥፍራ ገብተዋል፡፡ ክብራቸው የተገፈፈባቸው፣ የብርሃን ካባቸው የራቀቸው ነብሳት የአምላክን መምጫ በተስፋ ጠበቁት፡፡

ለዘላለም የማይጠፋውን ብርሃን ናፈቁት፤ ጨለማውን ስለሚያርቀው፣ ብርሃኑን ስለሚገልጠው፣ በሲኦል ያሉ ነብሳትን ስለሚያወጣው አምላክ ነብያት ትንቢት ተነበዩለት፣ የመምጣቱን ብስራት አስቀድመው ለዓለሙ ነገሩት፡፡ የነብያት ትንቢት በእውነት የእውነት የተነገረ ነበር እንጂ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ እርሱ በመጣ ጊዜ ሰውና መላእክት በአንድነት ይዘምራሉ፣ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ አምላክን ያመሰግናሉ፣ የተዘጉ በሮች ይከፈታሉ፣ በእሳት የሚገረፉ ነብሳት ከግርፋት ይወጣሉ፣ በድቅድቅ ጨለማ የታሠሩት ይፈታሉ፣ ገነት ትከፈታለች፣ ሲኦል ባዶዋን ትቀራለች፣ እየገረፈች፣ እያዳፋች የያዘቻቸውን ነብሳት ትቀማለች፣ ዓለም በብርሃን ትመላለች፡፡

ጌታ ኾይ ምድርን እያት፣ በቸርነትህ አስባት፣ በምረትህ ጎብኛት የሚሉት በዝተዋል፡፡ እንባቸውን የሚያፈስሱት፣ ስለበደላቸው ደረታቸውን የሚደቁት፣ የመከራውን ዘመን ለማለፍ የናፈቁት ተበራክተዋል፡፡ ዘመናት አለፉ፣ የጌታ ቃል ኪዳን የሚፈጸምበት ዘመን ደረሰ፡፡ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም ያለው አምላክ ቃሉን ሊፈጽም ምድርን ተመለከታት፣ በምህረት ዓይኑ አያት፤ በድላው ሳለ ሊክሳት፣ ርቀው ሳለ ሊያቀርባት፣ ትዕዛዙን አፍርሳ ሳለ ሊያስተምራት፣ ትዕዛዝም ሊያጸናላት ምድርን በፍፁም ፍቅር አያት፡፡

የጌታ መምጫው በደረሰ ጊዜ ለአምላክ ማደሪያነት የተዘጋጀች፣ ንጽሒት እና ብጽኢት የኾነች እመቤት በምድር ተገኘች፡፡ ከእያቄም እና ሃና ተወደለች፡፡ በምድር የካህናትን ዝማሬ፣ በሰማይ የመላእክትን ምስጋና እየሰማች አደገች፡፡ ይህችም እመቤት ለጌታ ማደሪያነት የተመረጠች፣ የዘላለሙን ንጉሥ ለመጸነስ የታደለች፣ በንጽሕና ተወልዳ በንጽሕና ያደገች ነበረች፡፡ የምህረት ዘመን ቀረበ፤ የመዳን ቀን ደረሰ፡፡

የእግዚአብሔር መላእክ ከሰማይ መጣ፡፡ ወደዚያች ንጽሒት እና ብጽኢት እመቤት ዘንድም ሄደ፡፡ ጸጋን የተመላሽ ኾይ ደስ ይበልሽ፣ እነኾ ትጸንሻለሽ፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ አላት፡፡ ትሑት ናትና በትሕትና ተቀበለችው፣ የጌታን ቃል በልቧ ጠበቀችው፡፡ መላእኩ ያላት ኾነ፡፡ ዓለም የማትወስነው፣ ምድር ቻይ ካልተባለች በስተቀር የማትችለው አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፡፡ በድንግል ማሕፀን አደረ፡፡

እርሱ እንደተጸነሰበት ማንም የተጸነሰ አስቀድሞ አልነበረም፤ ዘግይቶም አይኖርም፤ የእርሱ ልዩ ነውና፡፡ ለአምላክ ማደሪያነት የተመረጠች፣ የማይጠፋውን ብርሃን በማሕጸኗ የያዘች፣ እመቤት የመውለጀዋ ዘመን ደረሰ፡፡ አምላክ ፍቅሩን ሊገልጥ መጣ፣ የዘላለም ድኅነትን ሊሰጥ መጣ፡፡ ከአባቱ ሳይወጣ መጣ፣ ከአኗኗሩ ሳይለይ ወረደ፣ ከሦስትነቱ ሳይለይ መጣ፣ ከአንድነቱም ሳይለይ ወረደ፣ ከዙፋኑም ሳይለይ በስጋ ልጅ አደረ፣ ከምልዓቱ ሳይወሰን በማሕፀን ተፀነሰ፣ በላይ ሳይጎድል በማሕጸን ተወሰነ፣ በታችም ሳይጨመርበት ተወለደ እንደተባለ አምላክ ከሰማየ ሰማያት ከዙፋኑ ወረደ፣ ንጽሒት ከኾነች እናት ከቅድስት ድንግል ማርያም በቅድስና ተወለደ፡፡

መላእክት ቤተልሔምን ከበቧት፣ ቤተልሔምን ብርሃን መላት፣ በቤተልሔም የበራው ብርሃን ዓለምን አዳረሳት፡፡

ቤተልሔም የመንበሩ ከተማ ኾነች፣ አስቀድሞ ትንቢት የተነገረላት ቤተልሔም ጌታ ተወለደባት፣ ለዓለምም ብርሃኑን አበራባት፡፡ ቤተልሔም ከሁሉ የሚልቀው፣ መንግሥቱ የማይሻረው ዘመኑ የማያልፈው ንጉሥ ተወለደባት፡፡ እልፍ ከተሞች ነገሥታት ተወልደውባቸዋል፣ የተወለዱባቸው ነገሥታት ግን አላፊ ጠፊ ናቸው፡፡ ቤተልሔም ግን የነገሥታቱ ንጉሥ ተወለደባት፡፡

እርሷ ተመርጣለች የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በተጠራ ቁጥር አብራ ትጠራለች፡፡ በጨለማ የነበሩት በተስፋ የጠበቁት፣ ነብያት የተነበዩለት፣ ዘመናት የማይቆጠሩለት፣ ዓለማት የማይወስኑት ተወለደ። ሁሉ ያለው ምንም እንደሌለው በበረት ተወለደ፡፡ ከእርሱ አስቀድሞ የለም፣ እንደ እርሱ ያለ የለም፡፡ ሁሉ የእርሱ ነውና በቤተ መንግሥት በተወለደ ነበር፤ ባማረ አዳራሽም በተለወደ ነበር፣ ነገር ግን ትሑት ነውና ስለ ትሕትና በበረት ተወደለ፡፡

እርሱ በተወደለም ጊዜ ሰውና መላእክት በአንድነት ዘመሩ፣ በአንድነት አመሰገኑ፡፡ በተስፋ የጠበቁት መጣላቸው፣ የአዘኑትን የሚያጽናናው መጣላቸው፡፡
እነኾ ጌታ ተወልዷል፡፡ የሰው ልጅ ከባርነት ወጥቷል፣ በእርሱም ልደት ተቀድሷል፡፡

ትሕትና የተወለደው ዛሬ ነው፣ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ዛሬ ነው፣ ወንጌል የተወለደው ዛሬ ነው፣ የመንግሥተ ሰማያት በር የተከፈተው ዛሬ ነው፣ የበጎች እረኛ የተወለደው ዛሬ ነው፣ የዓለም መድኃኒት የተወለደው ዛሬ ነው፣ የአዘኑትን የሚያስደስተው የተወለደው ዛሬ ነው፣ እውነተኛው መብልና መጠጥ የተወለደው ዛሬ ነው፣ ለጨለማው ዓለም ብርሃን የወጣው ዛሬ ነው፣ የድሆች ፀጋቸው የተወለደው ዛሬ ነው። ተስፋ ላጡት ተስፋቸው፣ የድሃዎች አባታቸው የተወለደው ዛሬ ነው። የቆሸሹት የሚታጠቡበት ንፁሑ ውኃ የፈለቀው ዛሬ ነው ይላሉ አበው። ለምን ሁሉ ያለው፣ ሁሉን የሚያደርግ አምላክ ተወልዷልና፡፡
አምላክ ሰውን ለማዳን ሲመጣ በማርያም አድሮ መጣ፣ ሰውም ለመዳን ወደ አምላክ ሲሄድ ማርያምን አማላጅ አድርጎ ይሄዳል ይላሉ አበው፡፡ እርሷ ሰማይና ምድር የታረቁባት፣ የዓለም መድኃኒት የተገኘባት፣ በደል ያልተገኘባት፣ ፍጡር የማይስተካከላት፣ ሕዝብ ሁሉ መሰላል አድርጎ የሚወጣ የሚወርድባት ናትና።

ብርሃንን የፈጠረውን፣ ሰማይና ምድርን ያፀናውን፣ በክረምት የሚፈስሰው ማዕበል፣ በውቅያኖስ ያለው፣ በወንዞችም የሚወርደውን ውኃ በእፍኙ የማይሞላውን፣ የነፋስ አውታራትን የሚያዝዘውን፣ ዓለም ከመፍጠሩ አስቀድሞ የኖረውን፣ ዓለምንም አሳልፎ የሚኖረውን፣ ማንም ምንም የማይችለውን ቻለችው፣ ብርሃኑን ወለደችው፣ ወሰን የሌለውን ወሰነችው፣ የማይዳሰሰውን ዳሰሰችው፣ የማይቻለውን አዘለችው፣ ዓለሙን ሁሉ በቸርነቱ እና በምህረቱ የሚመግበውን አጠባቸው።
ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መላእክት የሚታዘዙለት፣ ከሰማይ እስከ ምድር እየረበቡ ስለ ክብሩ የሚሰግዱለት፣ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑት ፃድቃን የሚያገለግሉት አምላክ ለእናቱ ታዘዛት፣ ተራራዎችን የሚያዝዘው ታዘዛት፣ ዓለምን የሚያሳልፋት ታዘዛት፣ በፍፁም ትሕትና አገለገላት።
እነኾ ማይጠልቀው ብርሃን ወጥቷል፣ በዓለምም ብርሃን በርቷል፡፡ ከትሕትናው ትሕትናን፣ ከቅደስናው ቅድስናን ተማሩ፡፡

ክርስቶስ ሰውን በፍጹም ፍቅር እንደወደደ ሁሉ ሰውን ውደዱ፡፡ ክርስቶስ ተበድሎ ይቅር እንዳለ ሁሉ ይቅር በሉ፡፡ ʺመላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ እረኞቹ እርስ በርሳቸው እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ፡፡ የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ” እንዳለ መጽሐፍ ክርስቲያኖች በቤተልሔም የተወለደውን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በየዓመቱ በምስጋና እና በመዝማሬ ያከብሩታል፤ በረከትና ረድኤት ይቀበሉበታል፡፡ እነኾ ያ ቀን ደርሷልና የጌታን ልደት በምስጋና እያከበሩት ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!