“እስከ ህይዎት መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል” የምዕራብ ጎጃም ዞን የፖሊስ አባላት

0
56

“እስከ ህይዎት መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል” የምዕራብ ጎጃም ዞን የፖሊስ አባላት
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን የፖሊስ አባላት ለህልውና ዘመቻ የአንድ ወር ደሞዛቸውን የለገሱ ሲኾን ከመከላከያ፣ ከልዩ ኀይል እና ከሚሊሻው ጎን በመሠለፍ አሸባሪው ትህነግ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተጋረጠብን የህልውና አደጋ አኳያ የወር ደሞዛችንን መለገሳችን ቢያንስ እንጂ አይበዛም ያሉት የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ የሰው ኀይል ልማት አስተዳደር ዋና ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር ጠጅቱ ተስፋሁን ናቸው፡፡ ከመደበኛ የፖሊስ ተግባራት ባሻገር አሁን ላይ ጁንታው የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ግንባር ድረስ ለመዝመት እንደተዘጋጁም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሙስና ወንጀል ምርመራ ጥናትና ሃብት ማስመለስ ክፍል ኀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ ዮሐንስ በበኩላቸው አማራ ጠሉ የትህነግ ማፍያ ቡድን ግብዓተ መሬቱ እስኪፈጸም ድረስ ከወር ደሞዝ ባሻገር ግንባር በመሰለፍ ለመፋለም ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ከሕዝቡ ጋር በመኾን የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ሌት ከቀን እየሠሩ እንደኾነ የገለጹት ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ በቀጣይም ለሚሠጣቸው ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ እንደኾኑ አብራርተዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሁሉም የፖሊስ አባላትና የሲቪል ሠራተኞች የወር ደሞዛቸውን ለህልውና ዘመቻ ለመለገስ ቃል መግባታቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ቀለሙ አሰጋ ናቸዉ፡፡
የፖሊስ አባሉ ለህልውና ዘመቻ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በጦርነቱ ግንባር በመሠለፍ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋእትነትን ለመክፍል ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡
ዞኑ የአባይ ሸለቆን ተከትሎ የሚገኝ በመኾኑ ጁንታውና የጁንታው ተላላኪዎች ሰርገው በመግባት የሽብር ተግባር ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የተጠናከረ የበርና ኬላ ጥበቃ እየተደረገ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
የዞኑ ሕዝብ አካባቢውን በንቃት ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥረት መልካም ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው አሁንም ወጣቱና ሌላው ማኅበረሰብ አካባቢውን በንቃት እንዲከታተል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እስካሁን በተደረገው የአካባቢ ቁጥጥርና ክትትል በዞኑ 9 ጸጉረ ልውጥ ሰዎች በኅብረተሰቡ ጥቆማ ተይዘው 4ቱ በምርመራ ነጻ ሲለቀቁ ቀሪ 5 ሰዎች በማረሚያ ቤት ኾነው የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ይርጋ-ከፍኖ ተሰላም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here