“ኢንዶኔዥያዊያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት ዝግጁ ናቸው” የኢንዶኔዥያ አምባሣደር

230
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ደባርቅ:ጥር 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፣በጅቡቲና በአፍሪካ ኅብረት የኢንዶኔዥያ ሪፐብሊክ አምባሣደር አል ቡስይራ ባስኑር የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጎብኝተዋል።

አምባሣደሩ የፓርኩን ተፈጥሯዊ ገጽታ ከተመለከቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት “ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በማየቴ በጣም ተደስቻለሁ። በኢትዮጵያ ለአራት ዓመት ስቆይ እንደዚህ እምቅ የቱሪስት መስህብ በዚህ ቦታ አለ ብዬ አላስብኩም ነበር።ነገር ግን በጣም ውብና ማራኪ መኾኑን ዛሬ አረጋግጫለሁ” ብለዋል።

ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተፈጥሮ ውበት የምንዝናናበት ብቻ አይደለም ያሉት አምባሣደር አል ቡስይራ ጎብኝዎች አንዴ ወደ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከመጡ ብዙ ነገሮችን መሥራት ይችላሉ፤ሲፈልጉ አስገራሚ ፎቶዎችን መውሰድ፤ፊልም መሥራት፣ጥናትና ምርምምር ማድረግና ሌሎችንም መሥራት ይችላሉ ነው ያሉት።

አምባሣደሩ “ፓርኩን ከጎበኘሁ በኋላ ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያዊያን በተለይ በቱሪዝሙ በትብብር መሥራት እንዳለብን ተገንዝቤለሁ፤ከእኔ የፓርኩ ጉብኝት በኋላ በርካታ ኢንዶኔዥያዊያን ይሄንን ውብ ተፈጥሯዊ ቦታ መጥተው እንደሚጎበኙ ተስፋ አደርጋለሁም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኤንዶኔዥያ አምባሣደር እንደመኾኔ ለቤተሰቦቼ፣ለጓደኞቼ፣ለተከታዮቼና ለመላው ኢንዶኔዥያዊያን ስለተመለከትኩት ውብ ተፈጥሮና እምቅ የቱሪዝም ሐብት የማሳወቅ ግዴታ አለብኝ።እንዲጎበኙትም እጋብዛቸዋለሁ ብለዋል።

የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማሳደግና ለማስተዋወቅ ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ በጋራ መሥራት አለባቸው የሚሉት አምባሣሳደሩ ኢንዶኔዥያዊያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለዓለም ሕዝቦች ለማስተዋወቅ ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

ኢንዶኔዥያን ጨምሮ መላው ዓለም አስደናቂዉን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንዲጎበኙም በኢትዮጵያ፣በጅቡቲና በአፍሪካ ኅብረት የኢንዶኔዥያ አምባሣደር አል ቡስይራ ባስኑር መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ-አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!