ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሠራቸው የማነቃቂያ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

37

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሠራቸው የማነቃቂያ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል።

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከግል ዘርፉና ከኢንዱስትሪው ከፍተኛ አመራሮች፣ ከባለድርሻ አካላት፣ ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር የተደረገው ንቅናቄ አበራታች መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።

የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባካሎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አምራች ኢንዱስትሪውን እየደገፈ የሚሄድበት አካሄድ በጀመረው ልክ አዋጆችን እና ፖሊሲዎችን በማጠናቀቅ የተሻለ ሥራ ለመሥራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ምቹ ከማድረግ አኳያ ኢንቨስትመንት ስቦ ወደ ተግባር ከገቡ በኋላ ውጤታቸውን መለካት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ኢንዱስትሪው የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድምር ውጤት እንደመሆኑ የማኅበረሰብ አቀፍ ልማት በማሳተፍ ማስተሳሰር እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡትⵆ

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህልን ማዳበር እንደሚገባ፣ ለዚህ ደግሞ የብድር አገልግሎት ከሚመለከተው አካል ጋር በመቀናጀት መፍታት ይገባል ብለዋልⵆ

አባላቱ አክለውም በአምራች ኢንዱስትሪዎች እየገጠመ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ከውጭም ከውስጥም ካሉ አካላት ጋር ትስስሮችን በማጠናከር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋልⵆ

የሀገር ውስጥ ባለኃብት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በምርምር እና በጥናት መደገፍ እንደሚያስፈልግ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም እንደየዘርፋቸው ለማቀራረብ ችግሮችን በመለየት በቀጣይ ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ማብራራታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የውጭ ምንዛሬ ላይ የሚታየውን እጥረት ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ነው ያስረዱት።

ሚኒስትሩ አክለውም ኢንዱስትሪዎች ወደ ተግባር የገቡ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ስላለባቸው በቀጣይ ወደ ተግባር እንዲገቡ የማድረግ ተግባር ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋልⵆ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!