ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም አካታች እና ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስማርት የመማርያ ክፍል ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት አስረክቧል።
በመርሐ ግብሩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሃና እና የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ኩባንያው ሀገር አቀፍ የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የመማር ማስተማር ሂደቱ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚዋ አያይዘውም እየተከናወኑ የሚገኙ ሁለገብ ሀገራዊ ጥረቶችን ለመደገፍ ኩባንያቸው የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪ የስማርት የመማሪያ ክፍሉ መምህራን በቀላሉ ማስተማር እንዲችሉ፣ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶች በቴክኖሎጂ ቤተ-ሙከራ እንዲደገፉ፣ የትምህርት አሰጣጡን ከኹኔታዎች ጋር ለማጣጣም፣ የተማሪዎቹን ኹኔታ ለመከታተል፣ የምዘና ፈተናዎችን ለማረም እና ውጤቶችን ወዲያውኑ ለማሳወቅ እንዲሁም የተማሪዎችን የትምህርት መረጃዎች በቀላሉ ለማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ኢትዮ ቴሌኮም የትምህርት ዘርፉን ለማገዝ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መኾኑን ገልጸዋል። የስማርት መማሪያ ክፍሎቹ የትምህርት ዘርፉን አሠራር ያቀለዋል ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ሀገራዊ ተቋም የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ እና የተሻለ ትውልድ ለመገንባት በሚያደረገውን ጥረት ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡- እዮብ ርስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!