ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በመቋቋም እየሄደችበት ያለው የሰላም መንገድ ተመራጭ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡

0
52
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በመቋቋም እየሄደችበት ያለው የሰላም መንገድ ተመራጭ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ምክንያት በማድረግ በየ ጊዜው የሚነሱ ውጥረቶች ሲያንዣብቡባት ይስተዋላሉ፡፡ ኢትዮጵያም ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት አቋሟ መሆኑን ስታስገነዝብ ቆይታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ እያደረገችው ባለው ድርድርና የሰላም አማራጮችን መጠቀም በኩል የሚጠበቅባትን ምሁራን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት ክፍል መምሕር ዶክተር ተፈራ እሸቱ እንዳሉት ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ብዙ ጊዜ የጠብ መነሻ ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡ ሀገራትም የጠብ መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በውይይትና በድርድር መፍታት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በሱዳንና በግብጽ የሚነሱ የድርድር ሀሳቦች ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መሆኑንም ነው መምሕሩ ያስረዱት፡፡ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞችን መነሻ በማድረግ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ሁለት አንኳር ጉዳዮች እንዳሉ ያነሱት ምሁሩ እነሱም ሀገራት በፈቃዳቸው የሚያደርጉት ስምምነት እና ልማዳዊ ሕግ ናቸው ብለዋል፡፡
በሀገራት መካከል በፈቃደኝነት የተመሠረተ ስምምነት ከሌለ ልማዳዊ ሕግ ጥቅም ላይ እንደሚውል ዶክተር ተፈራ ጠቅሰዋል፡፡ ልማዳዊ ሕጉን ተጠቅመው ሀገራቱ በፍትሐዊና ምክንያታዊ መንገድ መስማማት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት የቦታ አቀማመጥን፣ የአየር ንብረት፣ ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን፣ የሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ፍላጎት ምን ይመስላል የሚለውን ከግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ግምት ውስጥ ሲገባ ደግሞ ኢትዮጵያ ተጠቃሚነቷ ሉዓላዊነቷን ባስከበረ መንገድ እንደሚሄድ ነው የጠቀሱት፡፡
በሱዳንና በግብጽ በኩል የሚነሱ ሀሳቦች በዓባይ ወንዝ ላይ የነበራቸውን የበላይነት የማስቀጠል ሂደት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስምምነት እንዳይደረስ ያደርገዋል ነው ያሉት ምህሩ፡፡ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚስማማበትን መርህ እስከመጨረሻው የመጠቀምና ለሕግ ያላትን ተገዢነት እያሳየች መሆኑንም አድንቀዋል፡፡
“እኔ ማንንም የመጉዳት ዕቅድ የለኝም፤ ተጎድቻለሁ የሚል ካለ ግን በሚችለው ሁሉ ያረጋግጥ” በማለት ኢትዮጵያ ከድርድሩ የመውጣት መብት እንዳላትም ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ተፈራ ኢትዮጵያ የተሻለ የመደራደር አቅም ያላት ሀገር መሆኗንም አንስተዋል፡፡ የሌሎች ሀገራት ተፅዕኖን በተመለከተም የሕግ መምሕሩ እንዳሉት ሀገራት ሌሎች ሀገራት ወደ ግጭት ሲገቡ ዝም ብሎ ማየት የለባቸውም፤ የማደራደር ኃላፊነት አለባቸው፤ በአንድ አካባቢ የሚፈጠረው ግጭት ለሁሉም ተፅዕኖ አለው፤ ችግራቸውን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲፈቱ የማድረግ ሚና አላቸው፤ ነገር ግን በሀገራት ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ የመግባት መብት የላቸውም፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ጫና ተቀባይነት እንደሌለው ዶክተር ተፈራ አስረድተዋል፤ ዓለም አቀፍ ሕግንም እንደሚጻረር ነው የገለጹት፡፡ ዶክተር ተፈራ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለውን የሰላም መንገድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲረዳትና እውነቷን እንዲያውቅ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ላይ ወደፊት የተሻለ ነገር ይገጥማታልም ባይ ናቸው፡፡
ዶክተር ተፈራ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ዋነኛው አማራጯ ውስጣዊ ሰላሟን ማስከበርና አንድነትን ማጠናከር መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟን መጠበቅ ከቻለች ማንም ኃይል ጫና ሊያሳድርባት አይችልም፡፡ አንድ ግድብ ብቻ በሌሎች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ማለት ስህተት ነው፤ ኢትዮጵያ ሌሎች ግድቦችን መገደብ አለባት፡፡ በያዘቸው ዕቅድ መሠረት ግድቧን መሙላትና መብቷን አሳልፋ እንዳትሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባታልም ነው ያሉት፡፡ የዓባይ ጉዳይ የሚቀጥለው ትውልድም ጉዳይ በመሆኑ ጥንቃቄው ከፍ ያለ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በጎንደር ዪኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምሕርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ባምላክ ይደግ (ዶክተር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራት ሰላም ዘብ የምትቆም ሀገር ናት፡፡ አንዲት ሀገር ችግር ሲገጥማት ያሉትን አማራጮች ሁሉ እስከመጨረሻው ድረስ መጠቀም አለባትም ነው ያሉት፡፡ ግጭቶችን ለማስቀረትና የሚደርሰውን ውድመት ለመቀነስ የሰላም አማራጮች አዋጭ ናቸውም ብለዋል፡፡
የዓባይ ግድብ ጉዳይ፣ የሱዳን ድንበር ላይ ወረራ እና ሌሎች ሀገራዊ ችግሮች ምክንያት ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅት ትዕግስትን የሚፈታተን እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ይህን ሁሉ በመቻል ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው መንገድ ትክክል መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የሰላም አማራጮችን መጠቀም እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ዶክተር ባምላክ ይደግ እንዳሉት የኃይል እርምጃዎች አስፈላጊ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚዎች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ግን የሰላም አማራጮችን መጠቀም ተመራጩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥራዎቿን አጠናክራ መቀጠል እንደሚገባት የተናገሩት ምሁሩ የዘመቻ ዲፕሎማሲዎች ጥቅማቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ጥቅም የላቸውምም ብለዋል፡፡
በተለያዩ ዓለማት ያሉ ዲፕሎማሲዎች ሥራቸውን በሚገባ መሥራትና እውነታውን ማስረዳት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ዶክተር ባምላክ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሉዓላዊነት መለኪያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here