ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ላይ የሚመክር የሁለት ቀናት መድረክ በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
ውይይቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ባላት ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዲሁም ችግሮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት ተወካዮች በምክክሩ እየተሳተፉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ (ዶክተር) ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ እና የፖሊሲ አቅጣጫ ለታዳሚዎቹ አብራርተዋል፡፡
የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታዋ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ደግሞ ለአፍሪካ ሠላማዊ አንድነትና ግንኙነት ኢትዮጵያ በትኩረት እየሠራች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡ የሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የሠላም ሁኔታ አቅጣጫ እንዲይዝ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ሚና ወይዘሮ አልማዝ በአብነት አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው የሠላም እና ደኅንነት ኮሚሽነር እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞው ዋና ጸሐፊ የደኅንነት ልዩ መልዕክተኛ ሰይድ ጄኔት በበኩላቸው የአንድ ሀገር ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዋናነት ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንጻር መቀረጽ እንዳለበት መክረዋል፡፡
ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያም ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ በተለይም ከኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጥንቃቄ መቅረጽ እንዳለባት ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ፎቶ፡- በጌትነት ገደፋው