“ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መስኩ የሚገጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ያደርጋል” የምዕራብ ጎጃም ዞን

93
ፍኖተ ሰላም:ጥር 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሀገር ያሉ ጸጋዎችን አሟጦ በመጠቀም ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንትን ይበልጥ በማዘመን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ “ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጀምሮ” ወደ ተግባር ተገብቷል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያም በአምራች ኢንዱስትሪዎችና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት ምርትን በጥራትና በብዛት በማሳደግ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ለማድረግ ያለመ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ በፍኖተ ሰላም ከተማ ተካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩ የተገኙ በዞኑ በተለያዩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ከተሰማሩ ባለሃብቶች መካከል በቡሬ ከተማ አስተዳደር በእንጨትና ብረታብረት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዘሪሁን ጥሩነህ መንግሥት “በኢትዮጵያ ታምርት” አዲስ ንቅናቄ በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን በመፍታት ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የሰጠው ትኩረት ሊበረታታ ሚገባው ነው ብለዋል።
በንቅናቄውም አካባቢያዊ ጸጋዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የሚያግዝ እውቀት ያገኙበት እንደኾነም ገልጸዋል።
መንግሥት አኹንም በባላሃብቱ የሚነሱ ችግሮችን ፈጥኖ ከፈታ ለውጥ ማምጣት ይችላል ነው ያሉት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ምንይችል ሽበሺ በዞኑ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚገጥሙ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት የአጋርና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማሳደግ ታላሚ ያደረገ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ መካሄዱን ተናግረዋል።
በንቅናቄው በዘርፉ እያገጠሙ የሚገኙ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ፣ባለሃብቱ የሚጠይቃቸውን የመሰረተ ልማትና የኀይል አቅርቦት ጥያቄዎች እንዲኹም የብድር አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት ኢንዱስትሪዎች በተሟላ አቅም ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ መድረኩ ቀላል የማይባል ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ መልካሙ ተሾመ፤ ዞኑ ካለው እምቅ አቅም አኳያ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ እድገት ወደ ኋላ የቀረ ነው ብለዋል።
መንግሥት ለዘርፉ እድገት ልዩ ትኩረት በማድረጉ አኹን ላይ ችግሮችን በመለየት ለውጥ ለማምጣት “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ ሚናው ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር ፣የምርት እድገት በማምጣት እንዲኹም ጠቅላላ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ሚናው ከፍተኛ በመኾኑ ለዘርፉ እድገትና መሻሻል ትኩረት በመስጥት ርብርብ የምናደርግበት ክፍለ ኢኮኖሚ ነው ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄም በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው መኾኑን ገልጸው መሰረታዊ ሃሳቡ የዘርፉን ተግዳሮቶች በመፍታት ምርትን በጥራትና በመጠን በማሳደግ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት እንደኾነም ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ይኼነው ዓለም በበኩላቸው የምዕራብ ጎጃም ዞን የበርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ሃብቶች ጸጋ ባለቤት በመኾኑ ይህንን በመጠቀም እና ቅንጅታዊ አሠራርን በማዳበር ዘርፉን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ 275 ባለሃብቶችና በአገልግሎትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 288 ባለሃብቶች መኖራቸውን ከዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፦ ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!