“ኢትዮጵያ በውጪ ኀይሎች መልካም ፈቃድ አትመራም” የሰላም ሚኒስቴር

0
93

“ኢትዮጵያ በውጪ ኀይሎች መልካም ፈቃድ አትመራም” የሰላም ሚኒስቴር

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገር ከሚያፈርሱ ኀይሎች ጋር እየተፋለመ መሆኑን ሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ በውስብስብ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እንዳሉም ተጠቅሷል፡፡ ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ተሻግራ ወረራ መፈጸሟም እንዱ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጥሩ የውጪ ኀይሎች በዋናነት ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ እንዳታካሂድ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ‘ኢትዮጵያን በታትነን የምንፈልገውን እናሳካለን’ ብለው የሚያስቡት እነዚህ ኀይሎች የሀገር ውስጥ ግጭቶችን እየደገፉ ነው፤ የብሔር ግጭት ለማስመሰልም ጥረት ማድረጋቸውን ነው በሚኒስቴሩ የሕግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ፍሬዓለም ሽባባው የገለጹት፡፡

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የታዩ ግጭቶች ከውጪ አመራር የሚሰጥባቸው እና በገንዘብ የሚደገፉ ሆነው እንደተገኙም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ባለፉት ጊዜያት የታዩ አብዛኛዎቹ የጸጥታ ችግሮች በውጪ ኀይሎች ድጋፍና አመራር ሰጪነት የተፈጠሩ መሆናቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

የእነዚህን ኀይሎች ሀሳብ ደግፈው የሚያስፈጽሙ የሀገር ውስጥ ‘ባንዳዎችም’ ተልዕኮ ተቀብለው መንቀሳቀሳቸውን ነው ሚኒስትር ዲኤታዋ ያስታወቁት፡፡ ሚኒስትር ዲኤታዋ እንደገለጹት የኢትዮያ መንግሥት መሰል ችግሮችን ተጋፍጦ የሀገር ሕልውናን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ሀገራዊ ምርጫውን እና የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት ለማከናዎን በቁርጠኝነት እየሠራ ነው፡፡ በሂደቱ ሊፈጠር የሚችል ነገርን ለመመከት ዝግጁ መሆኑን እና አሁንም እየመከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

“ኢትዮጵያ በውጪ ኀይሎች መልካም ፈቃድ አትመራም” ያሉት ምኒስትር ድኤታዋ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም እኩይ ዓላማዎች ለመመከት የሕዝቡ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከተባበሩ የውጪ ጣልቃ ገብነትን ማክሸፍ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

በለውጡ ማግስት የሀገርን ሰላም የማረጋገጥ ኀላፊነት ይዞ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር በጸጥታው ዘረፍ ስትራቴጂካዊ ፖሊሲዎችን የማውጣት ስልጣን በአዋጅ ተሰጥቶታል፡፡ የሀገሪቱን ሰላም የሚያረጋግጡ የጸጥታ ተቋማት እንደገና እንዲደራጁ፣ በጽንሰ ሀሳብ፣ በራዕይ፣ በአደረጃጀትና በሰው ኀይል አዲስ መልክ እንዲኖራቸው ማድረግም ከሚኒስቴሩ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በዚህ መነሻነትም በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች እንደተሠሩ ጠቅሰዋል፡፡ ቀደም ብሎ በፖለቲካ መሪዎች ይታዘዝ የነበረውን የፖሊስ ተቋም ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ እንዲሆን የተዘጋጀው ፖሊሲ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ እዲኖር፣ ያለምንም የጸጥታ ሥጋት በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ እንዲሠራ በሚያስችል መልኩ ሁሉንም የጸጥታ ተቋማት እንደገና ለማደራጀት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ወቅቱ በፈጠራቸው ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ሥራው ጎልቶ አልታየም ብለዋል፡፡ እነዚህ ውስብስብ ችግሮች ሕዝቡን ወዳልተፈለገ መንገድ ለማስገባትና በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሆን ተብለው የተሠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ለውጡ ካመጣው ችግር ጋር ተዳምሮ በተለይ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ አንዳንድ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል የሚቻል ቢሆንም በየክልሎቹ ቀድሞ የመተንበይና የመከላከል ውስንነት በመኖሩ ሕዝቡን ከጥቃት መታደግ እንዳልተቻለም አንስተዋል፡፡ ይህንን በዘላቂነት ለመፍታት፤ ችግሮች ለምን እንደተፈጠሩ፣ ማን እንደፈጠራቸው እና በምን መልኩ መመከት እንደሚቻል ግንዛቤ ለመፍጠር የሕዝብ ለሕዝብ የውይይት መድረክ ማካሄድ ተጀምሯል፡፡ ይህም ሕዝቡ የችግሮችን ምንጭ አውቆ እንዲመክት ያስችላል ተብሏል፡፡

በዚህም ተጨባጭ ለውጥ የመጣ መሆኑን በመጥቀስ ወደፊት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክልሎችን እየደገፈ በጸጥታ ዘርፍ አደረጃጀት ላይ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here