ኢትዮጵያ ስድስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች።

44

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዛምቢያ ንዶላ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያገኘችው የወርቅ ሜዳሊያ ብዛት ስድስት ደርሷል።
ዛሬ በሻምፒዮናው የአራተኛ ቀን ውሎ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች የ2 ሺህ ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር አትሌት አለምናት ዋለ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። አትሌት ፍሬህይወት ገሰሰ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ስታገኝ ፤አትሌት ሰላም ምህረት ስድስተኛ በመውጣት ውድድሯን አጠናቃለች።

አትሌት ዓለምናት ትናንት ከ20 ዓመት በታች ሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ወርቅ ያገኘች ሲሆን አትሌት ፍሬህይወትም በውድድሩ የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።
ዛሬ ማለዳ ላይ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች ወንዶች የ10 ሺህ ሜትር እርምጃ የፍጻሜ ውድድር አትሌት ምስጋና ዋቁማ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወቃል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው እስካሁን ያገኘችውን የወርቅ ሜዳሊያ ብዛት ስድስት አድርሳለች።
በተያያዘም ዛሬ ከ20 ዓመት በታች ወንዶች በተካሄደው የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ፍጻሜ አትሌት ያየህ አምሳሉ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ሲያገኝ አትሌት ሺመልስ ንጉሴ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮጵያ እስከ አሁን በሻምፒዮናው 6 የወርቅ፣7 የብር እና 3 የነሐስ በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ሁለተኛው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!