ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ምርጫ ያስፈልጋታል?

0
130
ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ምርጫ ያስፈልጋታል?
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደቱ ሠላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን መራጩ ሕዝብ፣ መንግሥት እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያነጋገርናቸው የደሴና የባሕር ዳር ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ለዘመናት በልጆቿ አጥንት እና ደም መስዋዕትነት በዓለም አደባባይ ታፍራ እና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ሃቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስርታ ሁሉንም ዜጎቿን በእኩልነት እና በፍትሐዊነት ማስተናገድ ግድ የሚላት ጊዜ ላይ ናት፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ባህል እና ልማድ አብዝቶ ለሚጫነው ማኅበረሰብ የምርጫን አማራጭነት የማስገንዘብ ሂደት ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡
በየትኛውም የሥራ መስክ እና የኑሮ ደረጃ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ከዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ባለፈ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ላይ ጉልህ አሻራም አለው፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊያን ምንም በማያውቁት ሥራ እና ሴራ ተወልደው ካደጉበት ቀያቸው “ውጡ፣ ልቀቁ” እየተባሉ የበዛ መከራና ግፍ የሚወርድባቸው፣ በሀገራቸው እንደባይተዋር የሚገፉበት ዋናው ምክንያት የክፋት እና የተንኮል ኃይሎች ዴሞክራሲን በጥላቻ፣ ኢትዮጵያዊነትን በአክራሪ ብሔርተኝነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን በዘርና በሃይማኖት ልዩነት ልክ ሸንሽነው “እኛ እናውቅላችኋለን” ስላሏቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ጌጥ በነበረው ልዩነታቸው የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደረጋቸው የዘር ልዩነት ከኢትዮጵያዊነት በላይ አብዝቶ በመሰበኩ ነው፡፡ አግላይ እና ነጣቂ የሆነው ሸረኛ የፖለቲከኞች ሴራ የሚቃናው ደግሞ በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት የሕዝብ ይሁንታን ባገኘ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚመኘው ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውን የሚሆነው ደግሞ በነቃ ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ ነው፡፡
በኢትዮጵያ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተረቅቆ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ አምስት ተከታታይ ሀገራዊ ምርጫዎች በየአምስት ዓመታት ልዩነት ተካሂደዋል፡፡ ነገር ግን ያለፉት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ከሂደታቸው እስከ ውጤታቸው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሕዝብ ይሁንታ ያልተስተናገዱባቸው እንደነበሩ ይተቻሉ፡፡
የኢትዮጵያን የምርጫ ታሪክ አስመልክቶ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ኤፍሬም ማዴቦ “ኢትዮጵያና ሕገ መንግሥታዊ ምርጫዎቿ” በሚለው መጽሐፋቸው ያለፉትን አምስት ተከታታይ ሀገራዊ ምርጫዎች ሲዳሰሱ “ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊነታቸው የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ሳይታወቅ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ከተካሄዱት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች በከፋ ሁኔታ የተከናወኑ ነበሩ›› ብለዋል፡፡
ቢያንስ በንጉሱ ዘመን የነበሩ ምርጫዎች የምርጫ ኮሮጆ የማይጭበረበርባቸው፣ ተመራጮቹም በተወከሉበት ምክር ቤት ሕዝብን የማይጠቅም የመሰላቸውን ውሳኔ ፀድቆ እንዳይተገበር የሚሞግቱ እና የሚሽሩ ነበሩ ብለዋል፡፡ እንደ ዘመነ ኢህአዴጉ ፓርላማ ከሕግ አስፈፃሚው አካል የቀረበለትን ሁሉ በሙሉ ድምፅ የሚያፀድቅ አልነበረም ይላሉ፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዓለማችን የወቅቱ የጤና ስጋት በሆነው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያክል ከተራዘመ በኋላ በመጭው ግንቦት መጨረሻ አካባቢ ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ ኢትዮጵያ ምን አይነት ምርጫ ያስፈልጋታል? ስንል አስተያየት ሰጭዎችን አነጋግረናል፡፡
ኢትዮጵያ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ ንግሥና የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤት፣ በዘመነ ደርግ ብሔራዊ ሸንጎ እና በዘመነ ኢህአዴግ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚል ምርጫ ይካሄድ ነበር ያሉን የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በየነ ፈንታው ናቸው፡፡ በሁሉም ምርጫዎች ላይ የሕዝብ ፈቃድ ተፈፅሞ ነበር ማለት ግን ይከብዳል ነው ያሉት፡፡
ከሁሉም በላይ “የፖለቲካ መስመሬ አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ነው የሚለው ኢህአዴግ እንደስሙ ሁሉ ዴሞክራሲን የምርጫ መርሁ የማድረግ ሰፊ እድል የነበረው ቢሆንም ሳይጠቀምበት እንዳለፈ ያወሳሉ፡፡
ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን የምዕራባዊያን ቀልብ መሳቢያ ብቻ አድርጎት ነበር ብለዋል አስተያየት ሰጭው፡፡ የምርጫ ሂደቱን ወከባ የበዛበት ማድረግ፣ በአምሳሉ የተፈጠሩ ተቃዋሚዎችን መፈልፈል፣ እውነተኛ ተፎካካሪዎችን በሰበብ አስባቡ ማሳደድ፣ ኮሮጆ ማጭበርበር እና ሲከፋም ብቻውን ማሸነፍ መለያው አድርጎት ነበር ሲሉ ይተቻሉ፡፡ ወደ መጨረሻ አካባቢም ሕዝብ በምርጫ ተስፋ ቆርጦ ገዥው ፓርቲ ብቻውን ሩጦ ብቻውን አሸንፎበትም ነበር ነው ያሉት፡፡
አቶ በየነ በምርጫ ተስፋ የቆረጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፍትሔ ወዳለው የኃይል አማራጭ የገባውም በምርጫ መንግሥት መቀየር እንደማይችል በማመኑ ነበር ብለዋል፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫም ካለፉ ስህተቶች ተምሮ የሕዝብን ፈቃድ ለመፈፀም መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል አቶ በየነ፡፡ ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫው ባለቤት ሕዝብ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥት ሂደቱን ግልፅ፣ የመወዳደሪያ ሜዳውን ምቹና ሰፊ ማድረግም ይጠበቅበታል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ለሀገር እና ለሕዝብ ይበጃሉ የሚሏቸውን አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን ማስተዋወቅ እና መራጩ ሕዝብም በመረጃ ላይ ተመስርቶ የሚበጀውን መምረጥ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
“ምርጫ የደኅንነት ስጋት እና የግጭት መንስኤ የሚሆንበት ዘመን ማክተም ይኖርበታል” ያለን ሌላው አስተያየት ሰጭ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ግዛቸው ደሳለኝ ነው፡፡ ወጣት ግዛቸው ሕዝብ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በበቂ መጠን መሠራት እንዳለበት ነው የጠቀሰው፡፡
የፓለቲካ ፓርቲዎች ለግጭት በር የማይከፍት የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ በአማራጭ ሃሳቦቻቸው እና ፖሊሲዎቻቸው ላይ ያተኮሩ ውይይቶች እንዲሁም የምርጫ ሕግን ያከበረ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባም አንስቷል፡፡
አስተያየት ሰጭዎቹ መጭው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንደሚጠናቀቅ እምነታቸው እንደሆነ ጠቁመው ሂደቱን ሠላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን መራጩ ሕዝብ፣ መንግሥት እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here