“ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው የመረጃ ጦርነት ለምዕራባዊያኑ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት መንገድ ጠራጊ ነው” ዶክተር አደም ጫኔ

100
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን ጦርነት የምዕራቡ ዓለም እይታ እና የሚያራምዱት አቋም መረን አልባ ነበር። ምዕራባዊያኑ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያራምዱት አቋም ፍጹም ተገቢ ካለመሆኑ በተጨማሪ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ የሆኑት ሚዲያዎቻቸው ደግመው እና ደጋግመው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሲዳፈሩ ተስተውሏል።

በዓለም ላይ ያሉት ዋና ዋና የብዙኀን መገናኛ ተቋማት እንደ አህጉር በአፍሪካ እንደ ሀገር በኢትዮጵያ በመረጃ ማዛባት ላይ አብዝተው የመጠመዳቸው ምስጢር ዘመናትን የተሻገረው የምዕራቡ ዓለም የሚዲያ ሕመም እና የፖለቲካ ሴራ ጋብቻ የወለደው ነው ብለው የሚያምኑ የዘርፉ ምሁራን አያሌ ናቸው። ሚዲያዎቻቸው፣ ፖለቲከኞቻቸው እና የእርዳታ ድርጅቶቻቸው የተናበበ፣ የተቀናጀ እና ቀጣይነት ያለው ዘመቻቸው ለሴራ ጋብቻቸው ማሳያ ተደርጎም ይቀርባል።

ትናንት በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጋራ ትብብር “የሐሰት መረጃ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ያሳደረው ጫና እና መፍትሔው” በሚል ሐሳብ የተካሄደው የምክክር መድረክ ጭብጥ ካደረጋቸው የመወያያ ነጥቦች አንዱም ይኸው በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው የምዕራባዊያኑ የመረጃ ጦርነት ነበር።

በምክክር መድረኩ ላይ “የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች በአፍሪካ ገፅታ እና በዲፕሎማሲው ላይ ያሳደሩት ጫና፤ የኢትዮጵያ ጦርነት እንደማሳያ” በሚል ርእስ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር አደም ጫኔ (ዶክተር) ናቸው። ዶክተር አደም በመወያያ ጽሑፋቸው የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ዘዋሪዎች ሚዲያውን የፖለቲካል ኢኮኖሚያቸው የበላይነት ማስጠበቂያ ተቋም እንዳደረጉት ገልጸው ሚዲያዎቹም የርዕዮተ ዓለማቸው ነጸብራቅ ሆነዋል ነው ያሉት።

የምዕራቡ ዓለም ያልተገባ ትርፍ የማጋበስ አባዜ አፍሪካን የትኩረት ማዕከሉ በማድረግ በተደጋጋሚ ሽጧታል ያሉት ዶክተር አደም ዓላማቸውም የፖለቲካ ልዩነት፣ የርዕዮተ ዓለም ውጊያ እና ያልተገባ የትርፍ ፍላጎትን መሰረት አድርጎ አህጎሪቷን የምዕራቡ ዓለም ጥገኛ ማድረግ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የመረጃ ጦርነት በዚሁ ማዕቀፍ እንደሚታይ የገለጹት ዶክተር አደም “ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው የመረጃ ጦርነት ለምዕራባዊያኑ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት መንገድ ጠራጊ ነውም” ሲሉ ገልጸውታል።

ዶክተር አደም በጽሑፋቸው “የምዕራቡ ዓለም ዞምቤዎች” ሲሉ የጠቀሷቸው እነዚሁ ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ የከፈቱት የመረጃ ጦርነት ግቡ ለአፍሪካ ነፃነት አርዓያ የሚሆን ሀገር እንዳይኖር ከመሻት የመነጨ ነው። የተቀናጀ፣ ተከታታይ የሆነ እና የተናበበ የመረጃ ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ እንደተከፈተ ገልጸው ተዋናዮቹም ከጋዜጠኞች እስከ ምሁራን፤ ከፓለቲከኞች እስከ ማኅበረሰብ አንቂዎች የተሳተፉበት ነው ብለዋል። አድሏዊ ሪፖርቶች፣ መሬት ላይ የሌሉ ትርክቶች እና አልፎ አልፎም የተዛቡና የተጋነኑ ዘገባዎች እንደሚሰራጩ አሳይተዋል።

የሚሰራጩት የተዛቡ መረጃዎች የአህጉሪቷን የዲፕሎማሲ አቅም ማሳጣት፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፍ ማዎክ፣ የተፈጥሮ ፀጋን አልምቶ ከድህነት እንዳይወጣ ለማድረግ እና የዜጎችን ሰብዓዊ ማንነት፣ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ገጽታ ማቀጨጭ የፈጠሩት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ማሳያ ተደርገው ቀርበዋል።

በሌላ በኩል የተፈጠረውን ዘርፈ ብዙ ፈተና ለመጋፈጥ ጫናን የመቋቋም አቅም ማደጉ፣ ሀገራዊ አንድነት መፈጠሩ፣ ወዳጅና ጠላት መለየቱ፣ ዲጂታል ሠራዊት መፈጠሩ እና በድጋሚ በፓን አፍሪካኒዝም ጥላ ስር ለመሰባሰብ መነሳሳት መስተዋሉ ቁጭት የወለዳቸው አዎንታዊ ጎኖች ተደርገው በዶክተር አደም ቀርበዋል።

ዶክተር አደም በመፍትሔ ሐሳባቸው የምዕራቡን ዓለም ሚዲያዎች ታሪካዊ ባላንጣነትና ውስብስብ አካሄድ መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የዲፕሎማሲ ትግሉን ማጠናከር እና ከምዕራቡ ዓለም የተለየ ርዕዮት ካላቸው ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራትን ምሁሩ በተጨማሪ በመፍትሔነት አቅርበዋል።

በቀረበው የመወያያ ጽሑፍ ላይ ምክክር ያደረጉት የጉባኤው ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የመረጃ ጦርነት ለመቀልበስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን #የበቃ ዘመቻ እና የዲጂታል ዲፕሎማሲውን በእውቀት፣ በክህሎት እና በቅንጅት ማገዝ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation