” ኢትዮጵያዊነት የሚገለጥበት፣ ግርማ የመላበትʺ

121
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ባሕር ዳር:ጥር 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፈጣሪ በአንበሳ አምሳል ተራራ ፈጥሮበታል፣ ከተራራው ግርጌ ጀግኖቹ ይመላለሱበታል፣ አይበገሬዎች ይሰባሰቡበታል፣ ስለ ሀገር ፍቅር ስለወገን ክብር ይመክሩበታል፣ የጸና ኢትዮጵያዊነት፣ የበረታ ጀግንነት፣ የማይፈታ አንድነት ይገለጥበታል፡፡
በዚያ ጀግኖች በሚፈጠሩበት፣ እንደ ጫካ አንበሳ በግርማ በሚኖሩበት፣ ተኩሶ መሳት በማይታወቅበት፣ ቃል ኪዳን በሚከበርበት ሥፍራ ፣ነፍስ የምትደሰትበት፣ ሐሴትም የምታደርግበት ነገር ሞልቷል፡፡ በዚያ ሥፍራ ጠላት የማይነጣጥለው አንድነት፣ እስከ ሞት የሚዘልቅ ታማኝነት፣ መከራ የማይበግረው ጀግንነት፣ ምላጭ የማያስብ አልሞ መችነት፣ የረቀቀ ሃይማኖት ሞልቷል፡፡ ሀገር ስትወረር፤ ሠንደቅ ስትደፈር ተቆጥተው ይነሳሉ፣ የመጣውን ጠላት ግንባር እየመቱ ይመልሳሉ፣ ምሽግ ተራምደው ምሽግ እያፈረሱ፣ አጥንት ከስክሰው ደም እያፈሰሱ ሀገር ያጸናሉ፣ ክብርን ያስጥብቃሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከተራራው በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፤ ሠንደቁን በኩራትና በክብር ያውለበልባሉ፡፡
ዕሁድ ቅዳሜ ኪዳን ያደርሳሉ፣ ቅዳሴ ያስቀድሳሉ፣ በአጸዱ ሥር ኾነው ዳዊት ይደግማሉ፣ ሰኞ ማክሰኞ ወደማሳው ወርደው በሰፊ ማሳ፣ በመልካም በሬ ያርሳሉ፣ ባረሱት ማሳ በሰፊ አውድማ ያፍሳሉ፣ የተራበን አንጀት በጮማና በፍርንዱስ ያረሰርሳሉ፡፡ የደከመውን ያሳርፋሉ፣ የታረዘውን ያለብሳሉ፣ ስሞት አፈር ስኾን እያሉ በቤታቸው ያቀማጥላሉ፡፡ በማሳዎቻቸው እሸት፣ በላሞቻቸው ወተት ሞልቷል፡፡
ክፉ ቀን ሲመጣ ዒላማ ጥለው የማይስቱ፣ ሰላም ሲመጣ ነጭና ጥቁር የሚያመርቱ፣ የክፉ ቀን ወታደሮች፣ የሰላም ቀን ገበሬዎች፣ ቀዳሽ፣ አስቀዳሾች፣ መካሪና ዘካሪዎች፣ አስራት በኩራት ከፋዮች፣ ሕግና ስርዓት አክባሪዎች፣ ብልሕ አርቆ አሳቢዎች ናቸው፡፡ አርሰውና ተኩሰው አይረኩም፣ በረሃ እያቋረጡ ይነግዳሉ፣ ነግደው ያተርፋሉ፣ ኹሉን ተችሯቸዋል እና በኹሉም ከፍ ከፍ ይላሉ፡፡ ጀግንነት፣ ሃይማኖት፣ አንድነት፣ የጸና ኢትዮጵያዊነት በመላበት በዚያ ሥፍራ በአምሳለ አንበሳ የተቀመጠ፣ ለበረከት ለቅድስና የተመረጠ፣ ሊቃውንት የሚፈልቁበት፣ ምስጢራት የሚመሰጠሩበት፣ ጥበብ የሚዘራበት፣ ቅዱሳን የሚኖሩበት፣ በረከት የማይታጣበት፣ ጠቢባን በጥበብ የሚመላለሱበት ውብ ሥፍራ አለ፡፡
ተራራው በተኛ አንበሳ አምሳል ተፈጥሯል፣ በቅድስና ተከብሯል፣ በመንፈስ ቅዱስ ተመልቷል፣ በእግዚአብሔር መልዐክ ይጠበቃል፡፡
በጥበብ የረቀቁ ሊቃውንት፣ ጥበብን ከአበው ሥር የቀስሙ ደቀመዛሙርት ነጥፈውበት አያውቁም፡፡ በዚያ ሥፍራ ዕውቀት እንደፈለቀ፣ ምስጢር እንደተመረመረ፣ ታሪክና ሃይማኖት እንደተነገረ ውሎ ያድራል፡፡ ጀንበር ዘልቃ በጠለቀች ቁጥር የአምላክ ስም ይጠራበታል፣ ይመሰገንበታል፣ የጽሕናው ድምጽ ይሰማሙበታል እስቴ መካነ ኢየሱስ፡፡
የጎንደር ነገሥታት በልዕልና የሚኖሩበት ዘመን ነበር፡፡ እኒያ ጠቢባን ነገሥታት ያማረውን ቤተ መንግሥት እየሰሩ፣ እያሰሩ፣ አድባራትን እያስደበሩ፣ ገዳማትን እያስገደሙ፣ ሀገራቸውን በጥበብ እና በብልሐት እያሰተዳደሩ ይኖሩ ነበር፡፡ ስማቸው በመልካም ሲነሳ ይኖር ዘንድ መልካሙን ነገር ያደርጋሉ፣ ለመልካም ነገር ይታትራሉ፡፡ ዘመኑ ከንግሥናቸው እኩል ቅድስናቸው የሚነገርላቸው ንጉሡ ዮሐንስ ( ጻዲቂ ዮሐንስ) የነገሡበት ዘመን ነበር፡፡ እሳቸውም ክብረ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ ዘውዳቸውን ደፍተው፣ በትረ መንግሥታቸውን ጨብጠው፣ በተሸለመው ፈረሳቸው ተቀምጠው፣ በፊት በኋላ፣ በቀኝ በግራ እንደ አንበሳ በጀገኑ እንደ ነብር በፈጠኑ ጀግኖች ታጅበው፣ በመኳንንቱ እና በመሳፍንቱ ተከበው ከቤተ መንግሥታቸው ይወጡ ነበር፡፡ እሳቸው ከንግሥናቸው ጋር ቅድስናቸውንም አጣምረው የያዙ ነበሩና በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ ጸሎት በማድረስ አምላካቸውን ያመሰግናሉ፣ ጥበቡን ይሰጣቸው፣ ሞገሱን ያሳርፍባቸው ዘንድ ይማጸናሉ፡፡
በዘመናቸው በእስቴ ዴንሳ በአምሳለ አምበሳ በተቀመጠው ተራራ ላይ ደብር ደበሩ፡፡ ደብሩም የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ነበር፡፡ የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አሥተዳደሪና የድጓ መምህር ሲሳይ አሰፋ እንደነገሩኝ ጻዲቁ ዮሐንስ ደብሩን ሲደብሩ በአማረውና በሚናፈቀው ተራራ ድንኳን ጥለው፣ ጸሎት እያደረጉ፣ አምላከቸውን እያመሰገኑ ነበር፡፡ የአፄ ዮሐንስ የንግሥና ዘመን በተፈፀመ ጊዜ አድያም ሰገድ ኢያሱ በዙፋኑ ላይ ተቀመጡ፡፡ እሳቸውም አፄ ዮሐንስ (ጻዲቁ ዮሐንስ) ድንኳን ጥለው ሲጽልዩበት የነበረውን ሥፍራ ጉልት አደረጉት፡፡
ዓድያም ሰገድ ኢያሱ በዚሕም ስፍራ ነገሥታቱ በክብር የሚወጡ የሚወርዱበት፣ ለተራራ መውጫ፣ ለሜዳ መሮጫ የሚኾኑ ፈረሶች ይረቡበት ዘንድ ወደዱ፡፡ መቶ ሃምሳ ፈረሶችንም በዚህ ሥፍራ እንዲራቡ አዘዙ፡፡ ያም ሥፍራ ፈረስ እየረባበት፣ ሽምጥ እየተጋለበበት፣ ጀግኖች እየወጡበት ዘመኑ ሄደ፡፡ የዓድያም ሰገድ ዘመን አልፎ፣ ዘመን ዘመንን እየተካ የንጉሡ ተክለ ጊዮሪጊስ ዘመን ደረሰ፡፡ በዚያም አስቀድሞ ርስትና ጉልት ኾኖ በቆዬው ሥፍራ የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተሠራ፡፡ ዓድያም ሰገድ ኢያሱ አባታቸው አፄ ዮሐንስ ባሰሩት የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን አጸድ ሥር ሲማሩ አድገዋል፡፡ ቤተ መቅደሱ በተጠናቀቀበት ጊዜ ከታቦተ ኢየሱስ በተጨማሪ ታቦተ መርቆሬዎስም አብሮ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ፡፡ በዚያ ዘመንም ጀምሮ በዓለ መርቆሬዎስ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት ይከበራል፡፡
በዚያ ሥፍራ አላፊውንና፣ መጭውን የሚያውቁ፣ በቅድስና የበቁ አበው ኖረውበታል፣ ደቀመዛሙርትን አፍርተውበታል፡፡ ዘመን ዘመንን እየተካ፣ ታሪክ እየቀጠለ፣ ኢትዮጵያ በጀግኖች እየተጠበቀች ቀጠለች፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነገሡበት ዘመን ደረሰ፡፡፤እሳቸው በነገሡበት ዘመንም ኢጣሊያ በዓድዋ ሰማይ ሥር የተሰበረ ቅስሟን፣ የተዋረደ ክብሯን፣ የጠፋ ስሟን ለማስመለስ ወረራ ጀመረች፡፡ በዚያም ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት የወራሪዋ ዒላማዎች ነበሩ፡፡ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያንም የኢጣሊያ ዒላማ ነበር፡፡ ለምን ከተባለ ታሪክ የሚነገርበት፣ ኢትዮጵያዊነት የጸናበት፣ ሃይማኖት የሚሰበክበት፣ ስለ ሀገር ፍቅር የሚወሳበት ነውና፡፡
የኢጣሊያ ወራሪዎች ወደ ሥፍራው ከመድረሳቸው አስቀድሞ አንድ የበቁ አባት ቤተክርስቲያኑ የመቃጠል አደጋ እንደሚደርስ ተናገሩ፡፡ ይሄን የሰሙ ካህናት ንዋዬ ቅድሳቱን አወጡት፡፡ በዋሻ ማርያምም ተጠለሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑም በወራሪዎች ተቃጠለ፡፡ በዚያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ታቦቱ የሚያርፍበት መንበር ነበር፡፡ ካህናቱም ንዋዬ ቅደስቱን ባወጡ ጊዜ ያን የታቦት ማረፊያ ረስተውት ነበር፡፡ አብሮም ተቃጠለ፡፡ ኢጣሊያ በጀግኖች አርበኞች ተቀጥቅጣ እንዳልነበረ ኾና ወጣች፡፡ በዋሻ ማርያም ተጠልለው የነበሩ ካህናትም ተመልሰው ወደ ቀደመው ሥፍራ አቀኑ፡፡
በዓለ ቅዱስ መርቆሪዎስም ደረሰ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ታቦቱ ሲወርድ ባልተቃጠለው መንበር ላይ ያርፍ ነበር፡፡ ካህናቱም ያ መንበር እንደተቃጠለ ስላወቁ ታቦቱን የት እናሳርፈው ይኾን እያሉ ተጨነቁ፡፡ አበውም ለታቦቱ ማረፊያ የሚሆን ለማዘጋጀት ወደ ታቦት ማደሪያው ወረዱ፡፡ በዚያም በደረሱ ጊዜ የሰው እጅ ያልፈነቀለው ድንጋይ አገኙ፡፡ ካህናቱም ፈቃዱ የእግዚዓብሔር እንደኾነ አወቁ፡፡ ታቦቱንም በዚያ ድንጋይ ላይ አስቀመጡ፡፡ ያም ድንጋይ ዛሬ ድረስ የታቦት መቀመጫ መንበር ኾኖ ያገለግላል፡፡ በዚያ ሥፍራ በርካታ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ ደናግላን፣ መዘምራን፣ ጳጳሳት እንደፈለቁበት መምህሩ ነግረውኛል፡፡ ጥበብን የሚነግሩ ሊቃውንት፣ ጥበብንም የሚሰሙ ደቀመዛሙርት በአጸዱ ሥር ታጥቶ እንዳማያውቅም ነግረውኛል፡፡ መጻሕፍት ይተረጉመበታል፣ ስርዓት ይሠራበታል፣ ታላቁና መልካሙ ነገርም ይደደረግበታል፡፡
ይህን ሊቃውንት የሚፈልቁበትን፣ ቅዱሳን የሚኖሩበትን፣ መንፈስ ቅዱስ የመላበትን ሥፍራ ካልዕት እስክንድሪያ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ እያሉ ይጠሩታል፡፡ የሃይማኖት የጸናበትና ከብሮ የኖረበት ነውና ደብረ ሃይማኖት ይሉታል፡፡ በዚሕ ስፍራ ከዓመት እስከ ዓመት ጸሎት እንደማይቋረጥበት፣ምሕላ የሚደረግበት ታላቅ ሥፍራ ነውም ብለውኛል፡፡
በዓለ ቅዱስ መርቆሪዎስ ደርሷል፡፡ ከአምሳለ አምበሳው ግርጌ ያለው ሜዳ በሰዎች ይመላል፤ ከዴንሳ ሰማይ ሥር ድንቅ ነገር ይታያል፡፡ ቀሳውስቱ፣ መነኮሳቱ፣ ዲያቆናቱ፣ አንባቢያኑና መዘምራኑ በልብሰ ተክህኖዓቸው ተጎናጽፈው ያረግዳሉ፣ በሰፊው ሜዳ ሲያዩዋቸው ከሰማይ ወረዱ መላዕክት ይመስላሉ፡፡ ምዕምናኑ እልል እያሉ በታቦት ማደሪያው ይሰባሰባሉ፣ አምላካቸውን እያመሰገኑ በደስታና በሀሴት ባሕር ውስጥ ይዋኛሉ፡፡
በዚያ ሥፍራ የእስቴ ጀግኖች፣ የፋርጣ ነብሮች፣ የጥናፋ አይበገሬዎች ፈረሶቻቸውን ሸልመው፣ ጦራቸውን አሹለው፣ የክብር ልብሳቸውን ለብሰው በክብር
ይገናኛሉ፡፡ አንደኛው ከሌላኛው ልቆ ለመገኘት፣ ኃያልነቱን ለማሳየት በፈረሶቻቸው ትንቅንቅ ይገጥማሉ፣ ከዳር ዳር ሜዳውን እያካለሉ ሽምጥ ይጋልባሉ፡፡ ከእነ ዓድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ጀምሮ በዚያ ሥፍራ ፈረስ ጉግስ እንደሚደምቅበት ይነገራል፡፡ በዚያ ያማረ ሜዳ የቀደመው ዘመን ይታወስበታል፣ የአኹኑ ዘመን ይታይበታል፣ የመጪው ዘመን ተስፋ ይጣልበታል፡፡
በዚያ የከበረ ሥፍራ ያለ ምክንያት እና ያለ መልዕክት የሆነ የለም፡፡ የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አሥተዳደሪና የድጓ መምህር ሲሳይ አሰፋ እንደነገሩኝ ታቦተ መርቆሪዎስ ወደ መንበረ ክብሩ ሲመለስ ሰባት ጊዜ ያርፋል፡፡ ሰባት ጊዜ ማረፉም አንድም የሰባቱ ዕለታት ምሳሌ፣ ሁለትም ማዕረጋተ ቤተክርስቲያንን ያዘክራል፡፡ መካነ ኢየሱስ ላይ ያለ ምክንያት፣ ያለ ትዕዛዝ የሚሆን የለም፣ አምላክ ያዘዘው ይፈጸማል፣ ሕግና ስርዓት ይጸናል፡፡ አበው ኑ በረከትን እና ክብርን ውረሱ፣ ሃይማኖትና ታሪክን ተማሩ፣ ሃብተ መንፈስ ቅዱስን ተጎናፀፉ ይላሉ፡፡ ሂዱ መልካሙን ነገር እዩበት፣ ታሪክ ተማሩበት፡፡ የተራራ ግርጌውን ድንቅ ነገር አድንቁበት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!