“ኢትዮጵያን ታድጌ ካልተሠራ ቤቴ መቼ ወልዳኛለች መክናለች እናቴ” ሊቀ መኳስ ያለው አዳነ

0
114

ጥቅምት 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የሃይማኖት አባት በፀሎቱ፣ ወታደር በሕይዎቱ፣ ጠቢብ በጥበቡ፣ ሲራራ በንግዱ፣ ልጅ በተተኪነቱ፣ አባት በአውራሽነቱ አንዱ ለሌላው እያቀበለ ትውልድ እንደ ሐረግ እያንሰላሰለ ያቆያት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀገር ናት፤ የቆመችውም በጋራ ትብብር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህያውነት ኢትዮጵያውያን ሁሉ በየዘመናቸው አቅማቸው በፈቀደው እና በተካኑበት ሙያ አበርክቷቸው የጎላ ነበር፡፡

በዘመናት መካከል ፈተና እና ጠላት አጥቷት የማታውቀው ኢትዮጵያ ከፈተናዎቿ ስትሻገር ይብዛም ይነስ ትውልዱ ሁሉ የየራሱ አበርክቶ ነበረው፡፡

ከውስጥም ከውጭም ጠላት እና ወጊ የማታጣው ኢትዮጵያ ዘላለማዊ ክብሯ እና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እንዲኖር ሕይዎታቸውን ያለስስት ከለገሷት ፋና ወጊ አርበኞች እና ወታደሮች በተጨማሪ እረኞች በመረጃ፣ እናቶች በደጀንነት እና ዓለም አጫዋቾች በሞራል የማይናቅ ሚና ስለመጫዎታቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡

ግንባሩን ለአሩር፣ ደረቱን ለጦር እና እግሩን ለጠጠር ከሰጠው ወታደር እና አርበኛ ጀርባ ቆመው የማሲንቋቸውን ጭራ እና የዋሽንታቸውን አንጓ ስሜት በሚነካ ቅኝት የሚነካኩት ሊቀ መኳሶች እና ዓለም አጫዋቾች ጥበባቸውን ለኢትዮጵያ ዘላለማዊ ክብር ያለስስት አውለዋል፡፡ በዚህም ሀገር እና ሕዝብ በሚገባቸው የክብር ማማ ልክ ያስቀመጣቸው ጀግኖች ብዙዎች ናቸው፡፡

ዛሬም በዚህ ዘመን አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልውና ላይ ሊረማመዱ ሲቃጣቸው ያ የጥንት የዓለም አጫዋቾች አበርክቶ በሰሜን ወሎዋ መቄት ወረዳ ገረገራ ከተማ “ነፍስ ዘርቶ ስጋ ነስቶ” አገኘነው፡፡

ዓለም አጫዎቹ ከማሲንቋቸው ጋር በተዋሃደው መረዋ ድምጽ

“ሲለው ማዶ ሲለው ማዶ፣
የጠላትን ምሽግ አደረገው ባዶ፤” ሲሉ ሰማናቸው፡፡ የ55 ዓመቱ ሊቀ መኳስ ያለው አዳነ የዓይናቸውን ብርሃን ባያጡ ኖሮ ከዚህ ሠራዊት ጋር በዱር በገደሉ እየወጡ እየወረዱ የሚወዷትን ሀገር ቢያገለግሉ ምንኛ በተደሰቱ ነበር፡፡ ድምጻቸው የእድሜያቸውን መግፋት አያሳብቅም፡፡ የአንገት ስሮቻቸው እስኪወጣጠሩ ድረስ ከጉሮሮ ብቻ ሳይሆን ከልብ በሚመነጭ ስሜታዊ ድምጻቸው የጥንቱን የአርበኞች ዘመን ተጋድሎ በእዝነ ሕሊናችን ያስቃኙናል፡፡

አዝማሪው ከተራራው ግርጌ ለኢትዮጵያ ክብር እና ዘለዓለማዊ ልዕልና ሕይዎቱን ሊሰጥ የወደደውን ወታደር እንዲህ ሲሉ ያሞገስታል፡፡
“እንኳን አሁን እና ሙሉ ትጥቅ እያለን፣
በጦር በጎራዴ ታንክ እንማርካለን፤” ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ታንክ እና ታንከኛ ቀርቶ ለወታደሩ በቂ መሳሪያ እንኳ ሳይኖረው በጦር እና ጋሻ ያለስስት ሕይዎቱን በደስታ እየሰጠ ታንክ ማርኮ ጠላትን በሃፍረት የሸኘ ነበር ብለዋል ሊቀ መኳስ ያለው፡፡ አሁን ያለው ወታደር እና ልዩ ኃይል ከጠላት የተሻለ እንጂ ያላነሰ ትጥቅ ይዞ ድል እንዴት ይጠረጠራል ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ መቄትን እና አካባቢውን ሲወር ጣራ ላይ የተሰቀለችው ማሲንቆ እና አልጋ ላይ የከረሙት አዛውንት ድል በመከላከያ ኃይል እጅ ስር ሲወድቅ ከአዲስ ዓመት መባቻ ጀምረው ወደ አደባባይ ወጥተው በአካባቢው ያለውን የወገን ጦር ለቀጣይ ድል ሲያበረታቱ እንደቆዩ ነግረውናል፡፡

ከዓድዋ እስከ ካራማራ፣ ከማይጨው እስከ መተማ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በድል ብሥራት ዜና መከራዎቻቸውን በአሸናፊነት ሲሻገሩ ከድሉ ፊት ለፊት በየዱር ገደሉ የወደቁ በርካታ ወታደሮች አሉ ብለዋል ሊቀ መኳስ ያለው፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና ሥጋት በድል ለመቀልበስ የአባቶቹን ወኔ እና ድል አድራጊነት ስሜት የተላበሰ ትውልድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

“ጠላት ምንጊዜም ጠላት ነው” የሚሉት ሊቀ መኳስ ያለው አዳነ ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ድምጽ እና በዘመናት ኑባሬ ባካበቱት የጥበብ ልምድ
“ድሮ አባቶቻችን ኢትዮጵያን ሲያቀኑ፣
እየተዋጉ ነው በዱር በገደሉ፤” በማለት የዚህ ትውልድ የታሪክ አደራ በእናንተ እና በወንድሞቻችሁ ተጋድሎ ይወሰናል ሲሉ ያበረቷቸዋል፡፡ የሕልውና ዘመቻውን የመጨረሻ የድል ብሥራት ዜና ለመስማት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጉጉት እንደሚጠብቅ በጥበባዊ ገለጻቸው ሊቀ መኳስ ይነግሯቸዋል፡፡ የሕልውና ዘመቻው ፍጻሜ እና ቀጣይዋ መዳረሻ ከሰሜናዊት ኢትዮጵያ ከተማ መሰረቱን እንደሚጥል ያበስራሉ፡፡ ይህ ባይሆን ግን የዘመናችን ኢትዮጵያ እንደ ጥንቱ ከአብራኳ ጀግና ማፍራት ያልቻለች መካን ትባላለች ሲሉም አምርረው ይመክራሉ እንዲህ እያሉ፡-

“ኢትዮጵያን ታድጌ ካልተሠራ ቤቴ
መቼ ወልዳኛለች መክናለች እናቴ”

በታዘብ አራጋው -ከገረገራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m